የአሰልጣኞች አስተያየት| ሲዳማ ቡና 2-1 መቀለ 70 እንደርታ 


በ 24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና በሜዳው መሪው መቀለ 70 እንደርታን አስተናግዶ 2-1 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

“ከእረፍት በፊት የቤት ስራችንን ጨርሰናል”
ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለጨዋታው

እስከ እረፍት አጥቅተን ለመጫወት ነበር የተጫወትነው፤ እናም ተሳክቶልናል። ከእረፍት በፊት የቤት ስራችንን ጨርሰናል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የጥንቃቄ ጨዋታ መርጠን በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ጎል ማግባት አልያም የያዝነውን ውጤት ለማስጠበቅ ነበር ያደረግነው። ከሞላ ጎደል ተሳክቶልናል እና በጣም ደስ ብሎኛል።

በሁለተኛው ግማሽ መበለጣቸው

ጫና እንደሚፈጠርብን እናውቅ ነበር። የመረጠንው የአጨዋወት ዘዴ እንዲጫወቱ ፈቅደንላቸዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ተጫውተዋል። ግን ወደእኛ ግብ በሚመጡበት ሰዓት ጎላችንን ጠብቀን ባገኘነው ኳስ ለመሄድ ነው ያሰብነው። የገባብን ጎል መግባት አልነበረበትም። ቢሆንም የጨዋታ ሁኔታ ስለሆነ ተቀብለነዋል።

የዋንጫ ፉክክር

የኛ አላማ ከፊት ለፊት ያሉትን ጨዋታ እያሸነፉ መሄድ ነው። ይህ ነገር ደግሞ ወደ ዋንጫው ያደርሰናል። ዛሬ ማሸነፋችን ወደ ዋንጫው ቀርበናል ሁለተኛ ደግሞ ወደ መሪው ቀርበናል። ስለዚህ ጥሩ ተነሳሽነትን ይፈጥርልናል።

” ጫና ውስጥ ሆነን ነው እየተጫወትን ያለነው”
ገብረመድህን ኃይሌ (መቀለ 70 እንደርታ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ከባድ ነው። ሲዳማ በሜዳው ጠንካራ እንደሆነ እናውቃለን። እውነት ለመናገር እዚ ለማሸነፍ ነው የመጣነው። ምክንያቱም ያለንን የነጥብ እና የመሪነት ደረጃ ማስቀጠል እንድንችል። ነገር ግን ራሳችን በሰራናቸው ስህተቶች በመጥፎ ሰዓት ግቦችን አስተናግደናል። ዘገየን እንጂ ጫና ፈጥረን መጫወት ችለናል። በእግር ኳስ ያጋጥማል ተሸንፈናል። በቀሩት ጨዋታዎች መሪነታችንን እናስጠብቃለን።

በመጀመሪያው ግማሽ መከላከላቸው

ከሜዳችን ውጭ እንደመጫወታችን የመጀመሪያ አጋማሽ አጨዋወታችን ቦታችንን ጠብቀን ኳስ በምናገኝበት አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት በፈጣን እንቅስቃሴ ማጥቃት ነበር። ነገር ግን አልሆነም። በሁለተኛው አጋማሽ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ማስገባታችን ተጭነን እንድንጫወት ረድቶናል። በመጨረሻ ደቂቃዎች ያመከናቸው ኳሶች ያስቆጫሉ።

ከሜዳ ውጭ በተደጋጋሚ ሽንፈት ማስተናገድ

እኛ ጫና ውስጥ ሆነን ነው እየተጫወትን ያለነው። ጫና ማለቴ ውጫዊ ጫናን ነው። ደጋግሜ ገልጫለው፤ ዳኝነቱ አሳማኝ አይደለም። የሚሰጡ ውሳኔዎች ወደ አንድ ወገን ያደሉ ናቸው። ዳኛዎቹም በነፃነት እያጫወቱ አይደለም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡