የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተካሂደዋል። ወልቂጤ መሪነቱን ሲያጠናክር ሐብታሙ ታደሰ ታሪክ ሰርቷል።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተጣለበት ቅጣት ምክንያት የማው ጨዋታውን ባቱ ላይ ያደረገው ወልቂጤ ከተማ ናሽናል ሴሜንትን 7-2 ማሸነፍ ችሏል። ሐብታሙ ታደሰ ለብቻው 6 ጎል ሲያስቆጥር አህመድ ሁሴን ቀሪዋን አንድ ጎል በስሙ አስመዝግቧል። ለናሽናል ሴሜንት ደግሞ ሙሉቀን አይርዳኝ እና ኤርሚያስ ቴዎድሮስ አስቆጥረዋል። በድሉ በመታገዝ ወልቂጤ በ3 ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል።
ሐብታሙ ታደሰ ሊጉ በ2008 ከተጀመረ ወዲህ በአንድ ጨዋታ 6 ጎሎች ያስቆጠረ የመጀመርያው ተጫዋች ሆኗል። በአጠቃላይ ዘንድሮ 9 ጎሎች ያስቆጠረው ሐብታሙ ሁሉንም ጎሎች ናሽናል ሴሜንት ላይ ማስቆጠሩ አስገራሚ አድርጎታል። (ሥስት በአንደኛ ዙር፤ ስድስት በሁለተኛ ዙር)
ኢትዮጵያ መድን በድጋሚ ነጥብ ጥሎ ከመሪው ርቋል። በሜዳው ሀላባን የገጠመው መድን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያይ ምስጋናው ወልደዮሐንስ ለመድን፤ ኤፍሬም ቶማስ ለሀላባ ከተማ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
ኢኮስኮ ተከታታይ ሽንፈት በነገሌ አርሲ አስተናግዷል። 1-0 በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ምትኩ ጌታቸው በ73ኛው ደቂቃ ብቸኛዋን የድል ጎል ለነገሌ አርሲ አስቆጥሯል።
ድሬዳዋ ፖሊስ በዲላ በሜዳው 3-0 ተሸንፏል። የዲላን የድል ጎሎች ፋሲል አበባየሁ በ28ኛው፣ ኤሊያስ እንድሪስ በ57 እና 74ኛው ደቂቃ የድል ጎሎችን በማስቆጠር ክለቡን ከወራጅ ቀጠናው አውጥተውታል።
የካ ክ/ከተማ የሁለተኛ ዙር መሻሻሉን ቀጥሎ በዚህም ሳምንትም ወላይታ ሶዶን 1-0 አሸንፏል። ንጉሱ ጌታሁን በ71ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
አዲስ አበባ ከተማ ከ ሀምበሪቾ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ለአዲስ አበባ ከተማ ኢብሳ በፍቃዱ 61ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር ለዘካርያስ ፍቅሬ በ90+5ኛው ደቂቃ ሀምበሪቾን አቻ አድርጓል።
ፎቶዎች – ወልቂጤ ይናቱ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡