ከፍተኛ ሊግ ሐ | ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ሲጥል አርባምንጭ ተጠግቷል


የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ጥሏል፤ አርባምንጭ፣ ጅማ አባ ቡና እና ሺንሺቾ አሸንፈዋል።

በሜዳው ነቀምት ከተማን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና 1-1 አቻ ተለያይቷል። ቴዎድሮስ መንገሻ በ4ኛው ደቂቃ እንግዶቹን ቀዳሚ ሲያደርግ አዩብ በቀታ በ30ኛው ደቂቃ ሆሳዕናን አቻ አድርጓል።

አርባምንጭ ከተማ በሜዳው ቡታጅራ ከተማን 2-1 አሸንፎ ከመሪው ያለውን ልዩነት አጥብቧል። ቴዲ ታደሰ በ50ኛው፣ ፍቃዱ መኮንን ደግሞ በ86ኛው ደቂቃ የአርባምንጭን ጎሎች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

በዕለተ ቅዳሜ ጅማ አባቡና ቤንች ማጂ ቡናን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። ከሜዳ ላይ እቅስቃሴ ይልቅ የጅማ አባቡና ደጋፊዎች በቡድኑ አመራሮች ላይ ያሰሙት ተቃውሞ የጎላ ነበር። ደጋፊዎቹ ተቋውሟቸውን ለአስር ደቂቃዎች ቦታቸው ላይ ባለመገኘት በየጨዋታው መሐል የቡድኑ አመራሮች ቡድኑ የገባበትን የፋይናንስ ችግር እንዲቀርፉ ጠንከር ያለ ተቋውሟቸውን አሰምተዋል። ባሳለፍነው ዓመት ቡድኑን የለቀቁት የክለቡን ፕሬዝዳንት ጨምሮ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ወደ ቡድኑ እንዲመለሱም ጠይቀዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቤንች ማጂዎች ኢሪክ ኮልማንን ትኩረት በማድረግ በግራና በቀኝ ከከማል አቶምና ከጌታሁን ገላዬ በሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶች ተደጋጋሚ እድሎችን ቢፈጥሩም ኳስና መረብን ለማገናኘት አልቻሉም። በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የፈለጉት ባለሜዳዎቹ በግራና በቀኝ መስመሮች አልፎ አልፎ የሚያደርጓቸው ሙከራዎች አደገኛዎች ነበሩ። በ12ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ የቤንች ማጂን የተከላካይ መስመር አምልጦ የወጣም ምስጋናው መኮንን ከግብ ጠባቂው ሌሊሳ ጋር ተገናኝቶ ሌሊሳ ቢመልስበትም ተከትሎት የገባው ጀላሎ ከማል ኳስና መረብን በማገናኘት ባለሜዳዎቹን አባቡናዎችን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ። ከግቡ መቆጠር በኃላ የጨዋታው ፍጥነትና በእቅስቃሴ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች መነቃቃት ተደጋጊ የግቡ ሙከራዎች ተደርገዋል በ15 ደቂቃ ጀላሎ ከማል ከርቀት የሞከረው የግቡን አግዳሚ ሲመልስበት በተመሳሳይ በ24ኛው ደቂቃ ከታዲዩስ አንበሴ ስህተት የተነጠቀች ኳስ ወንድማገኝ ኬራ ተከላካዮችን አልፎ ግብ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ የግቡን አግዳሚ መልሶ በድጋማ ከማል አቶም ያመከኗት አጋጣሚ ቤንች ማጂዎችን ወደ ጨዋታው ልትመልስ የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡ ከ29ኛው ደቂቃ በኃላም አባቡናዎች በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት በፉአድና በምስጋናው በተደጋጋሚ ያለቁላቸው አጋጣሚዎችን አግኝተው መጠቀም አልቻሉም፡፡

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ፉክክር ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም ሁለቱም ቡድኖች ተቀዛቅዘው ነው የቀረቡት። ቤንች ማጂ ሙሉ ለሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ቢጫወቱም ወደ ግብ በመድረስና እድሎችን መፍጠር ተቸግው ታይተዋል። በ77ኛው ደቂቃ ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ መሬት ለመሬት አክርሮ የመታው ኳስ ከመረብ ላይ በማሳረፍ ባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ አስቆጥሮ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጅማ አባቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች ከምባታ ሺንሺቾ በሜዳው ሻሸመኔ ከተማን 3-0 አሸንፏል። ናሆም አዕምሮ ሦስቱንም የድል ጎሎች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ በመስራት የዕለቱ ኮከብ ሆኖ ውሏል። 

ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከ ነገሌ ቦረና 1-1 ሲለያዩ አቤኔዘር ጥላሁን ለቢሾፍቱ፤ ምናሉ ተፈራ ለነገሌ ቦረና ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ስልጤ ወራቤ ከ ካፋ ቡና ያለ ጎል አቻ የተለያዩበት መርሐ ግብርም የዚህ ሳምንት አካል ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡