ደደቢት ቅጣት ተላለፈበት


በ23ኛው ሳምንት በትግራይ ስታድየም ደደቢት በፋሲል ከነማ 5-1 ባሸነፈበት ጨዋታ በተነሳው ረብሻ ባለሜዳው ደደቢት ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

ደደቢት በ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር በትግራይ ስታድየም ፋሲል ከተማን አስተናግዶ 5-1 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴም ከጨዋታው አመራሮች እንዳረጋገጠው የእንግዳው ቡድን ፋሲል ከነማ በማማሟቅ ላይ ሳለ ጀምሮ የመቐለ 70 እንደርታ መለያ በለበሱ ደጋፊዎች አፀያፊ ስድቦች እንደደረሰበት እና 64ኛው ደቂቃ ላይ አራተኛውን ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተጠባባቂ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ላይ የድንጋይ እሩምታ እንዳወረዱባቸው እንዲሁም ሦስት ተጨዋቾችም እንደተፈነከቱ ማረጋገጡን ኮሚቴው በቅጣት ደብዳቤው ላይ ገልጿል።

ሆኖም መቐለ 70 እንደርታ በስፍራው ውድድር ስላልነበረው እና ችግሩን የፈጠሩት ደጋፊዎችም የመቐለን መልያ ከመልበሳቸው ውጪ የክለቡን ፍላጎት ለማራመድ ስለመግባታቸው ማረጋገጫ ስለሌለ ተጠያቂ ማድረግ የማይቻል መሆኑን ኮሚቴው ገልጿል። በሌላ ወገን በቅድመ ጨዋታ ስብስባ ወቅት ደደቢትም ሆነ ፋሲል ደጋፊ እንደሌላቸው በማሳወቃቸው ባለሜዳው ክለብ ደደቢት ደጋፊ የለኝም እስካለ እና በስፍራው ለተገኙት ደጋፊዎችም ኃላፊነት እስካልወሰደ ድረስ ሜዳውን ለተመልካች ክፍት ማድረግ አልነበረበትም በሚል ጥፋተኛ አድርጎታል።

በዚህም መሰረት የዲስፕሊን ኮሚቴው ጥፋተኛ ያለው የደደቢት እግር ኳስ ክለብን ብር 150,000.00 እንዲቀጣ እና ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችንም በዝግ እንዲያከናውን ወስኖበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡