“ከውድድሩ ራሳችን ያገለልነው በገጠመን መጠነኛ የፋይናንስ ችግር ነው”  አቶ ተስፋይ ዓለም

በመጀመርያው ዙር ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር አልፈው የሚቀጥለው ማክሰኞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ለመጫወት መርሐግብር ወጥቶላቸው የነበሩት አዲስ አዳጊዎቹ ስሑል ሽረዎች ከውድድሩ ራሳቸው ያገለሉበት ምክንያት ትኩረታቸው ወደ ፕሪምየርሊግ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ባጋጠማቸው የፋይናንስ ችግር መሆኑን የቡድኑ ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋይ ዓለም ለሶከር ኢትዮጵያ ተናገሩ።

በጉዳዩ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የቡድኑ ፕሬዝደንት አቶ ተስፋይ ዓለም በቡድኑ ውሳኔ አስመልክተው ይህንን ብለዋል። ” የዓርቡን ጨዋታ ካደረግን በኋላ ባሉን ሁለት ቀናት ከመንግስት የምንጠብቀው ገንዘብ ነበር። እሱ በምፈልገው ሰዓት ስላልገባልን ነው ከውድድሩ ያገለልነው፤ ለፌደሬሽኑ በላክነው ደብዳቤም ይህንን ችግራችን ጠቅሰን ነው ከውድድሩ ያገለልነው። ”

” ከውድድሩ ራሳችንን ያገለልነው ለፕሪምየር ሊጉ ትኩረት ለመስጠት ነው በሚል በክለባችን ቡድን መሪ የተሰጠው መረጃ የተሳሳተ ነው። ከውድድሩ ያገለልነው በገጠመን መጠነኛ የፋይናንስ ችግር ነው” ብለዋል።

በሁለተኛው ዙር በርካታ ማሻሻያዎች በማድረግ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጥረት ላይ ያሉት ስሑል ሽረዎች ይህንን ውሳኔ መወሰናቸው ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በፎርፌ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ አረጋግጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡