ተጫዋቾቻችን በውጭ ሃገራት : ኡመድ ለኢኤንፒፒአይ መሰለፍ ጀምሯል

– አሚን አስካር ወደ ቀድሞ ክለቡ ሊመለስ ይችላል 

 

ያለፈውን ዓመት በግብፁ አል-ኢቲሃድ አሌክሳንደሪያ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፈው የፊት መስመር ተሰላፊው ኡመድ ኡኩሪ በአዲሱ ክለቡ ኢ.ኤን.ፒ.ፒ.አይ የመጀመርያዎቹ ጥቂት የሊግ ጨዋታዎች ካመለጡት በኃላ አሁን መሰለፍ ጀምሯል፡፡

 

ኡመድ በዘጠነኛ ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ኢኤንፒፒአይ ኤልሞካውሎን ኤል አረብን በፔትሮስፓርት ስታዲየም 3-1 ባሸነፈበት ጨዋታ ለ62 ደቂቃዎች መጫወት ችሏል፡፡

 

የኢኤንፒፒአይን የድል ግቦች መሃመድ ቃውድ፣ ራሚ ሳብሪ እና አህመድ ረፋት አስቆጥረዋል፡፡ ለእንግዳው ቡድን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ ታሂር መሃመድ በ65ኛው ደቂቃ በስሙ አስመዝግቧል፡፡

 

ሽመልስ በቀለ ፔትሮጀት ኢስማኤሊን አስ ስዎዝ ስታዲየም 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ተምልክቷል፡፡ የፔትሮጀትን የማሸነፊያ ግብ አህመድ ጋፍር ከመረብ አዋህዷል፡፡ ፔትሮጀት የአሰልጣኝ ለውጥ ካረገ በኃላ ያሳካው የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡ ፔትሮጀት የቀድሞ የፈርዖኖቹ ኮከብ አህመድ ሃሰን በገዛ ፍጋዱ ክለቡን ከለቀቀ በኃላ ታላት የሱፍን አዲስ አሰልጣኝ አድርጎ ሹሟል፡፡

 

ፔትሮጀት በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ ሰንጠረዥ በ8 ነጥብ 13ኛ ነው፡፡ የኡመዱ ኢኤንፒፒአያ በ13 ነጥብ 8ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

 

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ክለቡ ኤምሲ አልጀር በአልጀርስ ደርቢ ከዩኤስኤም አልጀር ያለግብ አቻ በተለያየበት የአልጀሪያ ሊግ 1 ጨዋታ ከቡድኑ ውጪ ሆኗል፡፡

ሳላ ከጨዋታው በፊት ተቀያሪ ሆኖ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ቢጠበቅም ሳይሳካ ከአልጀርስ ደርቢ ውጪ ሆኗል፡፡

በስታደ ጁላይ 5 1962 በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ዩኤስኤም አልጀር መሉ የጨዋታ ብልጫ ነበረው፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ዩኤስኤም አልጀር የአልጀሪያ ሊግ 1ን በ33 ነጥብ እየመራ ይገኛል፡፡ ኤምሲ አልጀር በ23 ነጥብ 3ኛ ነው፡፡

alger

በኖርዌይ የመጀመሪያ ሊግ ቲፕሊገን ለሚወዳደረው ሳርፕስቦርግ 08 ኤፍኤፍ የውድድር ዓመቱን በውሰት ያሳለፈው የመስመር አማካዩ አሚን አስካር ወደ ወደቀድሞ ክለቡ ኤስኬ ብራን ሊመለስ እንደሆነ ከኖርዌይ የሚመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

አሚን ብራንን ለቆ ሳርፕቦርግን በውሰት የተቀላቀለው በሚያዝያ 2015 ነበር፡፡ በሳርፕስቦርግ ቆይታው 27 ግዜ ተሰልፎ 2 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

ብራን ከአንደኛ ዲቪዚዮን ወደ ቲፕሊገን ማደጉ ለአሚን ወደ ክለቡ ለመመለስ መወስን ትልቁን ድርሻን ይወስዳል ተብሏል፡፡ አሚንን ይዞ የነበረው ሳርፕስቦርግ ቲፕሊገኑን 11ኛ ሆኖ ሲጨርስ የሊጉን ክብር ሮዘንበርግ አሳክቷል፡፡

 

የሱፍ ሳላ በስዊድን አንደኛ ዲቪዚዮን ለሚወዳደረው ኤፍሲ ዩናይትድ በመጫወት የውድድር ዘመኑን አሳልፏል፡፡ የመስመር አማካዩ በ15 ጨዋታ ላይ (5ቱን ከተጠባባቂ ወንበር ላይ በመነሳት) ለኤፍሲ ዩናይትድ ተሰልፎ ሲጫወት አንድ ግብ አስቆጥሮ ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተመዘውበታል፡፡  ክለቡ ኤፍሲ ዮናይትድም ሊጉን 8ኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡

 

ውጤት በደቡብ አፍሪካው ክለብ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ ጠፍቷል፡፡  ጌታነህ ከበደ ቋሚ ሆኖ በጀመረበት ጨዋታ አማተክስ በሱፐርስፓርት ዩናይትድ 2-0 ተሸንፎ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለመቆየት ተገዷል፡፡ ለሱፐርስፓርት ዮናይትድ ግቦቹን ማይክል ቦክስኦል እና ክሌይተን ዳኒኤልስ አስቆጥረዋል፡፡ ጌታነህ ከበደ በሁለተኛው አጋማሽ በታቦ ሞሳዲ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

 

አማተክስ በውድድር ዓመቱ መጥፎ አጀማመር ያሳየ ሲሆን አሰልጣኙ ሳሚ ትሮተን በቅርቡ ተሰናባች እነደሚሆኑ ብዙዎች ተንብየዋል፡፡ አማተክስ በአብሳ ፕሪምየርሺፕ በ6 ነጥብ 15ተኛ ሲሆን ሊጉን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በ26 ነጥቦች ይመራል፡፡

 

ዋሊድ አታ ባልተሰለፈበት የቱርክ ስፖር ቶቶ ሱፐር ሊግ ጨዋታ ገልሰንበርሊጊ በቱርኩ ሃያል ክለብ ፌነርባቼ 1-0 ተሸንፏል፡፡ የፈርናንዶ ግብ ፌነርባቼ ሙሉ ሶስት ነጥብ እንዲወስድ በቂ ነበረች፡፡

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ገልሰንበርሊጊ በ13 ነጥብ 16ኛ ሲሆን ቤሲክታሽ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል፡፡

 

ዋሊድ አታ እስካሁን ድረስ ባለው የቱርክ ቆይታው እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገው ቃለ-ምልልስ በቅርብ ቀን ይዘን እንቀርባለን፡፡

ያጋሩ