ቅድመ ጨዋታ ዳሳሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ወላይታ ድቻ

በነገው ዕለት በትግራይ ስቴድየም ወልዋሎ እና ወላይታ ድቻ የሚያገናኝውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ባለፉት ጨዋታዎች በወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ጉዳት እና በሥነምግባር ጉድለት ምክንያት እንደ ተጋጥሚ ቡድን አቀራረብ ተቀያያሪ የጨዋታ ስልት መርጠው የተጫወቱት ቢጫ ለባሾቹ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኃላ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆኑ እና በርካታ ተጫዋቾች ከጉዳት መልስ ማግኘታቸውን ተከትሎ ቡድናቸው ላይ ለውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በባለፉት ጨዋታዎች በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች የተጫዋቾች ምርጫቸው የተገደበው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በነገው ጨዋታ ቡድኑ ጥሩ በነበሩባቸው ወቅቶች ምርጥ ብቃቱ ሲያሳይ የነበረው አማኑኤል ጎበናን ጨምሮ ደስታ ደሙ ፣ ሬችሞንድ አዶንጎ እና ክሪስቶፈር ችዞባን ማግኘታቸውን ተከትሎ ወደ ውጤታማው 4-4-2 አሰላለፋቸው የሚመለሱበት ዕድል የሰፋ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት የሜዳቸው ጨዋታዎች ከተለመደው ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ወጣ ብለው ሁለቱ የመስመር ተጫዋቾች በተሻለ ማጥቃቱ ላይ ሲያሳትፉ እና ለወትሮው ወደ ተከላካይ ቀርበው የሚጫወቱት ሁለቱ የመከላከል ባህሪ ያላቸው አማካዮች ወደ አጥቂ አማካዮች ቀርበው እንዲጫወቱ ሲያደርጉ የቆዩት ወልዋሎዎች የነገው ተጋጣሚያቸው ወላይታ ድቻ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚያጠቃ ቡድን እንደመሆኑ በቡድናቸው የቦታ አያያዝ ላይ መጠነኛ ለውጥ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት ደደቢት ወደ ሶዶ ባለማምራቱ ምክንያት በፎርፌ ካሸነፉበት ውጪ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ማግኘት ተስኖአቸው ወደ ወራጅ ቀጠናው ይበልጥ የተጠጉት ወላይታ ድቻዎች በሊጉ ለመቆየት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ያለምንም ጉዳት እና ቅጣት የሚያፋለሙበትን ይህን ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። በሜዳቸው ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፉበት ጨዋታ በኃላ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ የጣሉት የጦና ንቦቹ በጨዋታ አቀራረብ ከሚመሳሰሏቸው ወልዋሎዎች ሶስት ነጥብ ወስደው ከተከታዮቻቸው ያላቸውን ልዩነት ማስፋት አስበው እንደሚገቡ ይጠበቃል። ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው ጨዋታዎች አፈግፍገው የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ፍጥነት መሰረት ያደረገ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለመተግበት የሚሞክሩት የጦና ንቦች በነገው ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው የጨዋታ አቀራረብ እና ከጨዋታው ወሳኝነት አንፃር ጥንቃቄ ላይ ከተመሰረተ አጨዋወት ይልቅ ከባለፉት የሜዳ ውጭ አቀራረብ በተለየ አጥቅተው ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– አምና ወልዋሎ ወደ ሊጉ ካደገ ጀምሮ ያደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ በ1-1 ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።

– ትግራይ ስታድየም ላይ 12 ጨዋታዎችን ያደረገው ወልዋሎ አምስቴ ድል ሲቀናው ሁለት ሽንፈት እና አምስት የአቻ ውጤቶች ገጥመውታል።

– ከሶዶ በወጣባቸው 13 ጨዋታዎች ድል ቀንቶት የማያውቀው ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰውም አምስት ጊዜ ብቻ ነበር።

ዳኛ

– ጨዋታው ለፌድራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ የዓመቱ አራተኛ ጨዋታው ይሆናል። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው ጨዋታዎች ስምንት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አንዴ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተጫዋች ያስወጣ ሲሆን አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-4-2)

ዓብዱልአዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – በረከት አማረ – ደስታ ደሙ – ብርሃኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – ብርሃኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ – ኤፍሬም አሻሞ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ራችሞንድ አዶንጎ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

መኳንንት አሸናፊ

እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ዐወል አብደላ – ሄኖክ አርፌጮ

በረከት ወልዴ

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ቸርነት ጉግሳ

ባዬ ገዛኸኝ – አላዛር ፋሲካ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡