ፕሪሚየር ሊግ – ድሬዳዋ ከነማ ከሜዳው ውጪ ድል ሲያስመዘግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ ድሬዳዋ ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ባንክ በሜዳው ነጥብ ጥሏል፡፡

ቦዲቲ ላይ ድሬዳዋ ከነማን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 1-0 ተሸንፏል፡፡ የእንግዶቹን የድል ግብ በ44ኛው ደቂቃ ከመረብ ያሳረፈው ፍቃዱ ታደሰ ነው፡፡ ፍቃዱ ባለፈው ሳምንትም ድሬዳዋ ሆሳዕናን እንዲያሸንፍ የረዳችውን ወሳኝ ግብ ከመረብ ማሳረፉ የሚታወስ ነው፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-0 በማሸነፍ ነገ ከሚጫወተው አዳማ ከነማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቧል፡፡ የፈረሰኞቹን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፉት ራምኬ ሎክ እና አዳነ ግርማ ናቸው፡፡ ቀልብ ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች በክለቡ ማልያ አሸብርቀው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ታይተዋል፡፡ በአሰልጣን ማርት ኑይ ደስተኛ ያልሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደግሞ አሰልጣኙ ላይ የተቃውሞ ድምፅ አሰምተዋል፡፡

11፡30 ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ንግድ ባንክ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ ሲዳማ ቡና በ74ኛው ደቂቃ በአጨቃጫቂ ሁኔታ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት በአንዱአለም ንጉሴ አማካኝነት በማስቆጠር መምራት ቢችሉም አንተነህ ገብረክርስቶስ ከማእዘን ምት የተሻገረችውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ንግድ ባንክን አቻ አድርጓል፡፡

የ6ኛ ሳምንት 3 ጨዋታዎች ነገ ሲደረጉ አዳማ ከነማ ዳሽን ቢራን ፣ መከላከያ ሀዋሳ ከነማን በተመሳሳይ 9፡00 ላይ ያስተናግዳሉ፡፡ ደደቢት ኪኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ 11፡30 ላይ ይካሄዳል፡፡

የደረጃ ሰንጠረዡን አዳማ ከነማ በ13 ነጥቦች ሲመራ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የደደቢቱ ሳሚ ሳኑሚ በ5 ግቦች ይመራል፡፡

ያጋሩ