ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ ስሑል ሽረ

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉት ጨዋታዎች ሁለት ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በትግል ላይ ያሉ ቡድኖችን የሚያገናኘውን ተጠባቂው ጨዋታ የዳሰሳችን የመጨረሻ ትኩረት አድርገነዋል።

በሁለተኛው ዙር በተመሳሳይ በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት በወራጅ ቀጠና የሚገኙ ሁለት ክለቦች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ከሌሎች የሳምንቱ ጨዋታዎች በበለጠ ተጠባቂ ነው። አዳማ ከተማን ካሸነፉበት ጨዋታ ውጪ በተቀሩት አራት የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አቻ የተለያዩት ደቡብ ፖሊሶች ምንም እንኳ ያለፉትን ጨዋታዎች ውጤታቸው እምብዛም ጥሩ ባይሆንም ከተጋጣሚዎቻቸው ጥንካሬ አንፃር ሲታይ ግን ቡድኑ ምን ያህል እንደተሻሻለ ማሳያ ናቸው። በተለይም በእልህ አስጨራሹ የባህር ዳር ጨዋታ እና ወደ ጎንደር እና አዲስ አበባ አምርቶ ከፋሲል እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጋቸውን ጨዋታዎች ነጥብ ይዞ መመለሱ ጥሩ ጉዞ ላይ የመሆኑ ማሳያዎች ናቸው። የጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት የሆኑት ደቡብ ፖሊሶች በቅርብ ጊዜያት ጥሩ የግብ ማግባት ክብረ ወሰን ያለው የስሑል ሽረ የማጥቃት ክፍል የሚጠብቃቸው ፈተናም በጨዋታው ተጠባቂ ጉዳይ ነው። ደቡብ ፖሊሶች ከአጥቂያቸው ይተሻ ግዛው ቀላል ጉዳት ውጪ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለባቸውም አጥቂውም በጨዋታው ሊሰለፍ የሚችልበት ዕድል እንዳለም ታውቋል።

በሁለተኛው ዙር በተሻለ ብቃት ላይ የሚገኙት ስሑል ሽረዎች ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው ጨዋታዎች መጥፎ ክብረ ወሰን ቢኖራቸውም ይህ ጨዋታ ከቅርብ ተቃናቃኛቸው እንደመሆኑ በብዙዎች ከተገመተው ውጤት ውጪ ሊመዘገብ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው። ሁለቱም ፈጣን የመስመር ተከላካዮች በብዛት የሚያሳትፈው የመስመር አጨዋወት ለመተግበር የሚሞክሩት እንግዶቹ በዛሬው ጨዋታ እንደባለፉት ጨዋታዎች ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ቡድኑ የመስመር አጨዋወቱን ባይቀይርም የመስመር ተከላካዮቹ እንቅስቃሴ ሚዛናዊ ማድረጉ ግን አይቀሬ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሁለት ወሳኝ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾቻቸው አሳሪ አልመሃዲ እና ደሳለኝ ደባሽ ያጡት ስሑል ሽረዎች ክፍተቱን ለመሸፈን በመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ለውጥ ለማድተግ የሚገደዱ ይመስላል። ሰንደይ ሮትሚ ፣ ሀፍቶም ቢሰጠኝ ፣ አሳሪ አልመሃዲ እና ዮናስ ግርማይ በጉዳት የማይሰለፉ የእንግዶቹ ተጨዋቾች ሲሆኑ የደሳለኝ ደባሽ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ያገናኛቸው የ10ኛው ሳምንት ጨዋታ በ 1-1 ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።

– በአዲስ አበባ ስታድየም ከድቻ ጋር የተገናኘበትን ጨዋታ ሳይጨምር ሀዋሳ ላይ 12 ጨዋታዎችን ያደረገው ደቡብ ፖሊስ አራቴ ድል ሲቀናው በቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ግን ምንም ነጥብ ማሳካት አልቻለም።

– ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ 11 ጨዋታዎችን ሲያደርግ በአንድ ድል እና በሁለት የአቻ ውጤቶች አምስት ነጥቦችን ቢያሳካም ስምንት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– አስር ጨዋታዎችን ዳኝቶ 43 የቢጫ ካርዶችን እንዲሁም አራት ቀጥታ ቀይ ካርዶችን የመዘዘው እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ ከዚህ ቀደም ደቡብ ፖሊስ ከቡና እንዲሁም ሽረ ከመከላከያ እና ድቻ ጋር የተገናኙባቸውን ጨዋታዎች ዳኝቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ዳዊት አሰፋ

ዓብዱሰላም አማን – ክብሮም ብርሃነ – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ረመዳን ናስር

ብሩክ ተሾመ – ሀብታሙ ሽዋለም

ቢስማርክ አፖንግ – ያስር ሙገርዋ – ቢስማርክ አፕያ

ሳሊፉ ፎፋና

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

አናጋው ባደግ – ደስታ ጌቻሞ  – ዘሪሁን አንሼቦ – አበባው ቡታቆ

 ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ኪዳኔ አሰፋ

ብርሀኑ በቀለ – ኄኖክ አየለ – ብሩክ አየለ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡