ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ሀዋሳ ከተማ

በነገው ዕለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል የሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ ሃዋሳ ከተማን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከሜዳቻው ውጪ ማሸነፍ ተስኗቸው ከተከታዮቻቸው ጋር የነበራቸው ሰፊ የነጥብ ልዩነት ማስጠበቅ ባለመቻላቸው አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት 70 እንደርታዎች በሜዳቸው ካላቸው የማሸነፍ ክብረ ወሰን እና ከተጋጣሚያቸው ወቅታዊ አቋም አንፃር የተሻለ የማሸነፍ ግምት ይሰጣቸዋል። ባለፉት ጨዋታዎች በተለዋዋጭ አቀራረብ ጨዋታቸው ያደረጉት መቐለዎች በአመዛኙ በሜዳቸው ላይ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከሚከተሉት አጨዋወት ብዙም የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ባይጠበቅም ጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ጋናዊው አጥቂ ኦሴይ ማውሊ አሁንም ከጉዳት ባለመመለሱ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ማሻሻያዎች ሊደረጉ ይችላሉ። አጥቂው በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በቀጥተኛ አቀራረብ ውጤታማ የማጥቃት ጥምረት ፈጥረው የነበሩት ምዓም አናብስት የረጅሙ አጥቂው አለመኖር ከቀጥተኛ አጨዋወቱ ውጪ ሌላ አማራጭ እንዲያዩ ያስገድዳቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ቡድኑ ወደ ቀድሞ የመስመር አጨዋወት እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። በባለሜዳዎቹ በኩል ከአጥቂው ኦሴይ ማውሊ ህመም ባለፈም ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ መሰለፉ አጠራጣሪ ሆኗል።

ከመልካም አጀማመር በኃላ ቀስ በቀስ መንሸራተት አሳይተው በሰንጠረዡ አጋማሽ ያሉት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ አዳማ አቅንተው ካገኙት ሦስት ነጥብ ውጪ ሌላ የሜዳ ውጪ ድል ባይኖራቸውም በዚህ ጨዋታ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ያልቻሉት ሀይቆቹ አብዛኞቹ ተከታዮቻቸው በጥሩ ብቃት ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ ነጥባቸው ከፍ ማድረግ ካልቻሉ በቀጣዮቹ ሳምንታት አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ስለማይቀር ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ይላቸዋል። ከሁለቱም መሰመሮች በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች እና ከአማካዩ ታፈሰ ሰለሞን እንቅስቃሴ መነሻነት ለማጥቃት የሚሞክሩት ሀዋሳዎች ባለፉት ጨዋታዎች ውጤታማ ያላደረጋቸው እና በርካታ ጎሎች ያላስቆጠሩበት ዓመቱን ሙሉ የተከተሉት አጨዋወት ይቀይራሉ ተብሎ ባይጠበቅም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው ግን የተጫዋቾች ቅያሪ እንኳ ባይደረግባት ጠንካራው የመቐለ የማጥቃት አጨዋወት ለመመከት የቅርፅ ለውጥ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ ቅጣት ያስተላለፈበት ታፈሰ ሰለሞንን ይዞ ወደ መቐለ ያላመራ ሲሆን በአንፃሩ ገብረመስቀል ዱባለ ከጉዳት አገግሞለታል።

የእርሰ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– መቐለ ወደ ሊጉ ከመጣበት የአምናው የውድድር ዓመት ጀምሮ ሦስት ጊዜ ሲገናኙ መቐለ ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ የ 1-0 ድሎችን ሲያሳካ አንድ ጊዜ ያለግብ ተለያይተዋል።

– ትግራይ ስታድየም ላይ 14 ጨዋታዎችን ያከናወነው መቐለ 70 እንደርታ 12 ጊዜ አሸንፎ ሁለቴ አቻ ተለያይቷል። ከጨዋታዎቹ በሰባቱ ግብ ሳያስተነግድ ከሜዳ መውጣት ችሏል።
– ሀዋሳ ከተማ ካደረጋቸው 12 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ አራቴ ነጥብ መጋራት የቻለ ሲሆን ሁለት ጊዜ ደግሞ በድል ተመልሷል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የዓመቱ 14ኛ ጨዋታውን ይዳኛል። ከዚህ ቀደም መቐለን ከድቻ ሀዋሳን ደግሞ ከሲዳማ ጋር ያጫወተው አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው ጨዋታዎች 43 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ 2 የቀይ ካርድ እና 3 የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ70 እንደርታ (4-2-3-1)

ሶፈንያስ ሰይፈ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተስማ – ክዌክ አንዶህ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል መሐመድ – ሚካኤል ደስታ

ያሬድ ከበደ – ሃይደር ሸረፋ – ሳሙኤል ሳሊሶ

አማኑኤል ገብረሚካኤል

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ወንድማገኝ ማዕረግ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – አክሊሉ ተፈራ – ሄኖክ ድልቢ– ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡