የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ 0-0 ወላይታ ድቻ

ትግራይ ስታድየም ላይ የተካሄደው ጨዋታ ያለጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የአሰልጣኞች ጨዋታ ነበር ጨዋታው” አሸናፊ በቀለ

ስለ ጨዋታው

ለመሸናነፍ የተደረገ ትግል ነው። በሁለታችን መሃከል ጥረ የመሸናነፍ እንቅስቃሴ ታይቷል። ሁሉም ማሸነፍ ነው የሚፈልገው። እርግጠኛ ነኝ ወልዋሎዎችም ማሸነፍ ነው የሚፈልገው። እኛም አስበን የመጣነው ማሸነፍን ነው። ምክንያቱም ያለንበት ደረጃ የሚያኩራራ ስላልሆነ በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ነበር የፈለግነው። ያገኘናቸው የግብ አጋጣሚዎች አልተጠቀምንም ባጠቃላይ ግን መልካም ነው።

ጨዋታው በታክቲክ የታጠረ ነበር። ዮሃንስ ሳህሌም በዚ የታወቀ ነው። ሁለታችን ታክቲኩ ላይ ጥሩ ስለነበርን ጥሩ ተናበናል ማለት እችላለው። እኔ እሱ ያሰበው ነገር ተረድቻለው፤ እሱም ያሰብኩትን ነገር ተረድቷል። የአሰልጣኞች ጨዋታ ነበር ጨዋታው።

“ደጉ እና ተስፋዬ በልምድ ቡድናቸውን ይዘው ወጥተዋል” ዮሃንስ ሳህሌ

ስለ ጨዋታው

ነጥቡን ይዘው ለመሄድ ያሰቡ ነበር የሚመስለው እሱንም አሳክተዋል። በሰዓቱን በመግደል ጨዋታው እንዲቋረጥ እና ከቅኝታችን እንድንወጣ በማድረግ ነጥብ ተጋርተው ነበር መሄድ የፈለጉት፤ ያንንም አሳክተው ሄደዋል።

ውጤቱ ጨዋታውን ይገልፀዋል?

እኛ ወደ ጥሩ ቅኝት በምገባበት ግዜ ይወድቃሉ ፣ ሰዓት ይገድላሉ ተጎዳው ይላሉ። ልምድ ያላቸው እንደነ ደጉ ደበበና ተስፋዬ አለባቸው ያሉ ተጫዋቾችም ስላሏቸውም የኛ ጨዋታ ገብቷቸዋል። ተጭነን መጫወት ስንጀምር ያቋርጡታል። በአጠቃላይ እነ ደጉ እና ተስፋዬ በልምድ ቡድናቸው ይዘው ወጥተዋል ታሪኬም ጨምሮ። እኛም ከራሳችን የሚጠበቀው አላደረግንም ያንን ምክንያት ሊሆን አይችልም ሙሉ በሙሉ ፤ እኛ ብዙ ማድረግ ያሉብን ነገሮች ማድረግ አልቻልንም ብዙ ኳስ አበላሽተናል መሃል ሜዳ ላይ።

አንድ ቡድን ልታሸንፈው የምትችለው ከፍቶ ሲጫወት ነው። ዘግቶ ከተጫወተና ነጥብ ለማስጣል ከሆነ ሰብረህ ለመግባት አስቸጋሪ ነው ምክንያቱ ዓላማው ማሸነፍ ሳይሆን ዘግቶ መጫወት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡