በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በሲዳማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ቡና ሽረ ላይ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ክሪዝስቶም ንታንቢ እና ሳምሶን ጥላሁንን በማሳረፍ በምትካቸው ወንድይፍራው ጌታሁንን እና አማኑኤል ዮሃንስን አሰልፏል። በተመሳሳይ ሳምንት መቐለን ከረታበት ቡድን የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረገው ሲዳማ ቡና በመሳይ አይኖ እና ይገዙ ቦጋለ ቦታ ፍቅሩ ወዴሳ እና መሀመድ ናስርን ተጠቅሟል።
ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ሀብታሙ ገዛኸኝ ከወንድይፍራው ጌታሁን ባስጣለው ኳስ አደጋ መፍጠር ችለው የነበሩት ሲዳማዎች ፈጣን አጀማመር ቢያደርጉም ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ቀስ በቀስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ያደላ እንቅስቃሴ ያደረጉባቸው ነበሩ። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ አስፈሪነት ይታይባቸው የነበረው መሀል ላይ ኳስ በሚያስጥሉባቸው አጋጣሚዎች ብቻ ነበር።
ከሲዳማ በተሻለ ቅብብሎችን በመከወን መሀል ሜዳውን ሲሻገሩ ይታዩ የነበሩት ቡናዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ ከቀኙ የሳጥን ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታው ኳስ በፍቅሩ እቅፍ ከተያዘበት ውጪ የግብ ዕድሎችን በብዛት ማግኘት አልቻሉም። ይልቁኑም ወደ ሳጥኑ በሚቀርቡባቸው አጋጣሚዎች ጥረታቸው ወደ ሙከራነት ከመቀየሩ በፊት ኳሶች ይበላሹባቸው ነበር። 23ኛው ደቂቃ ላይ ሻባኒ ወደ ግራ ካደላ ቅጣት ምት በቀጥታ ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት ሌላው የቡድኑ የተሻለ ሙከራ ሆኖ መጠቀስ ይችላል። ቡናዎች ተሳክቶላቸው በቅብብል ሳጥን ውስጥ በገቡበት የ29ኛ ደቂቃው አጋጣሚም ግማሽ ጨረቃው አካባቢ ከተቀባበሉት ኳስ በቀኝ በኩል ከግብ ጠባቂ ጋር የመገናኘት አጋጣሚ የነበረው ሻባኒ ሙከራው በፍቅሩ ወደሳ ድኖበታል።
በራሳቸው የግብ ክልል ለመቆየት የተገደዱት ሲዳማዎች ኳስ የሚይዙባቸው ጊዜያት የሚያደርጉትም ቅብብል ከሜዳቸው ሲወጣ አይታይም። በብዛት ከፊት ተነጥለው ይታዩ የነበሩት ሦስቱ አጥቂዎቻቸውም ከቅብብሉ ርቀው ረጃጅም ኳሶችን ይጠባበቁ ነበር። 26ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሀንስ በድንገት የላከው ረጅም ኳስም ለሀብታሙ ጥሩ አጋጣሚን ቢፈጥርለትም ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ሲዳማዎች የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ላይ ሦስቱን አጥቂዎች ከኳስ ጋር ከቡና የተከላካይ ክፍል ፊት ያገናኙ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ቢያገኙም በጨዋታ ውጪ እንቅሳሴ እና በቅብብል ስኬት መውረድ ሳቢያ ውጤታማ መሆን አልቻሉም። እየተቀዛቀዘ የሄደው እና የዳኛ ፊሽካ የተበራከተበት አጋማሽም ያለግብ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሀብታሙ ገዛኸኝን ወደ መሀል መሀመድ ናስርን ደግሞ ወደ ቀኝ መስመር አጥቂነት የለወጡት ሲዳማዎች ወንድሜነህ ዓይናለም መሀል ላይ በዳዊት ተፈራ ተቀይሮ ከመግባቱ ጋር ተደምሮ የተሻለ ጫና መፍጠር ችለዋል። ያም ሆኖ መሀመድ ከቀኝ አቅጣጫ በመነሳት ወደ ውስጥ ያደርጋቸው የነበሩ የጎንዮሽ ሩጫዎች በቅቅብሎች የታገዙ አልነበሩም። 63ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ተጨዋቹ ከዚሁ አቅጣጫ ለግቡ ቅርብ ለነበረው አዲስ ግዳይ ጥሩ ኳስ ቢያቀብልም አዲስ በቶሎ ባለመወሰኑ በተከላካዮች ተቀምቷል። በሌላ አጋጣሚ 67ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ከሳጥን ውጪ ያደረገው አደገኛ ሙከራም ለጥቂት ነበር ወደ ውጪ የወጣው።
ኳስ በሚይዙባቸው አጋጣሚዎች ወደ ፊት ገፍተው ለመጫወወት ይጥሩ የነበሩት ባለሜዳዎቹ በቶሎ የመከላከል ቅርፃቸውን ይይዙ የነበሩት ሲዳማዎችን አልፈው ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ታይተዋል። ይልቁኑም ያልተደራጀው የማጥቃት መንገዳቸው ለአደገኛው የሲዳማ ቡና መልሶ ማጥቃት አጋልጧቸዋል። 70ኛው ደቂቃ ላይም አዲስ ግደይ በመሀል ሜዳው የግራ ወገን ላይ ሆኖ በረጅሙ ከደረሰው ረጅም ኳስ ያስጀመረውን ድንገተኛ ጥቃት በፍጥነት ሳጥን ውስጥ በመገኘት ከወንድሜነህ ዓይናለም መልሶ በመቀበል ቀለል አርጎ ጨርሶ ሲዳማን መሪ አድርጓል።
ከግቡ በኋላ ባለሜዳዎቹ ግብ ለማግኘት እንግዶቹ ደግሞ ውጤት ለማስጠበቅ ያለመ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ነገር ግን ቡናዎች በቅብብሎች ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ሳጥኑ አቅራቢያ ሲደርሱ እየተበላሸ ረጃጅም ኳሶቻቸውም ውጤታማ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ጠንካራ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። 75ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ የኋላሸት ፍቃዱ ከቅጣት ምት ተከላካዮች የተደረቡትን ኳስ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ አክርሮ ሲመታ ፍቅሩ አውጥቶበታል። ሲጠብቁት የነበረውን ሌላ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ያገኙት ሲዳማዎች በአንፃሩ አጋጣሚውን እንዲሁ አላለፉትም። ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ያመሸው ሀብታሙ ገዛኸኝ አዲስ የመጀመሪያውን ጎል ጥቃት ካስጀመረበት ቦታ ላይ ከወንድሜነህ የደረሰውን ኳስ ሳጥን ድረስ በመግፋት ገብቶ ወደ ውስጥ አቀበለ ሲባል አክርሮ በመምታት የሲዳማዎችን ድል እርግጥ አድርጎታል። በጭማሪ ደቂቃ አማኑኤል በተከላካዮች መሀል የሰጠውን ኳስ የኋላሸት ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ቢሞክርም ፍቅሩ እንደምንም አድኖበት ኢትዮጵያ ቡና ውጤቱን ማጥበብ ሳይችል ጨዋታው ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡና ባሳካው እጅግ ወሳኝ የሜዳ ውጪ ድል አዲሱን የሊጉን መሪ ፋሲል ከነማን በሦስት ነጥቦች መከተሉን ሲቀጥል ወደ ሁለተኝነት ዝቅ ካለው መቐለም ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት ዝቅ አድርጓል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡