በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛው ሳምንት ሀዋሳ ላይ በወረጅ ቀጠና ውስጥ ያሉትን ደቡብ ፖሊስ እና ስሑል ሽረን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ደቡብ ፖሊሶች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ነጥብ መጋራት ከቻሉበት ስብስብ ውስጥ የዘነበ ከድር እና የተሻ ግዛውን ቦታ በአበባው ቡታቆ እና ብሩክ ኤልያስ የተኩ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳቸው ድል ያደረጉት ስሑል ሽረዎች ደግሞ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል፡፡ በዚህም ደሳለኝ ደበሽ ፣ ዮናስ ግርማይ እና ቢስማርክ ኦፖንግ አርፈው በምትካቸው ዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ ፣ ክብሮም ብርሀነ እና ሐብታሙ ሸዋለም ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
ስሑል ሽረዎች ፍፁም የእንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራ ብልጫን በወሰዱበት የመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ አጋጣሚዎች የፈጠሩ ሲሆን የደቡብ ፖሊሱ ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ ብቃት ግን በቀላሉ መረቡን የሚያስደፍር አልሆነም፡፡ ቢጫ ለባሾቱ በአንፃሩ የዘላለም ኢሳያስ በመሀል ሜዳው መቀዛቀዝ እና በሚሰሯቸው የቅብብል ስህተቶች ተጋላጭ ለነበረው የመከላከል ክፍላቸው መጠቃት ምክንያት ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን በተጋጣሚያቸው የሙከራ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ፖሊሶች ገና የጨዋታው ፊሽካ እንደተነፋ ነበር ወደ ሽረ ግብ ክልል መድረስ የቻሉት። በግራ በኩል 3ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ኤልያስ ከዘላለም ጋር በፈጠሩት ጥምረት የተገኘችዋን ጥሩ ዕድል አበባው ቡታቆ በቀጥታ ቢመታም በግቡ አናት ወጥታበታለች፡፡ የሳሊፍ ፎፋናን አስፈሪ የማጥቃት ሂደት ለመግታት የተቸገሩት ፖሊሶች የአጥቂውን እንቅስቃሴ በቀላሉ መገደብ ሳይችሉ ቶሎ ቶሎ ከሙሉዓለም ረጋሳ እግር ስር ከሚነሱ ኳሶች ይበልጡኑ ሲጠቁ ታይተዋል፡፡ 6ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ አፒያ አመቻችቶ ሰጥቶት ብልጠቱን በመጠቀም ሳሊፍ የፖሊስ ተከላካዮችን አልፎ ከግብ ጠባቂው መክብብ ጋር ተገናኝቶ መክብብ በግሩም ሁኔታ የያዘበት አጋጣሚም በዚህ ውጥ የሚጠቃለል ነው። መክብብ ሳሊፍ ፎፋና ከቢስማርክ ተቀብሎ የሞክረውን ሌላ ኳስም በአስደናቂ ሁኔታ አድኖበታል።
ከተሻጋሪ ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የተገደዱት ባለሜዳዎቹ በሚሰሯቸው ስህተቶች በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው ቢሆንም በተለይም በግራ በኩል ወጣ ገባ ያለ ማጥቃት ለመሰንዘር ሞክረዋል።
በ14ኛው ደቂቃ ብርሀኑ በቀለ ወደ ውስጥ ኳስ እየነዳ በመግባት ክፍት አቋቋም ላይ ለነበረው ሄኖክ ሰቶት ሄኖክ ሲመታው ዲሚጥሮስ ከግቡ ጠርዝ ላይ ተንሸራቶ ወደ ውጪ አውጥቶበታል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላም ዘላለም ከማዕዘን ሲያሻማ ዮናስ በርታ በግንባር ገጭቶ ዳዊት አሰፋ ወደ ውጪ ያወጣበት ሊጠቀሱ ሚችሉ ሙከራዎች ናቸው፡፡
በሌሎች ሙከራዎች 20ኛው ደቂቃ ጉዳት እስካስተናገደበት ድረስ ከሙሉአለም ረጋሳ ጋር ጥምረቱ የተሳካ የነበረው ያስር ሙገርዋ በቀኝ በኩል ዘሪሁን አንሼቦን አልፎ የሰጠውን ኳስ ሳሊፍ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም መክብብ በግሩም ሁኔታ መልሶበታል፡፡ ጫናቸው በማሳደሩ የተዋጣላቸው ሽረዎች በቀኝ በኩል ወደ ሳጥን ገብቶ በቀጥታ የመታውን ኳስ በጨዋታው ከደጋፊዎች አድናቆት ሲቸረው የነበረው የደቡብ ፖሊሱ ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ በድጋሚ ይዞበታል፡፡ 28ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ሸዋለም ከማዕዘን ምት ሲያሻግር ደስታ ጌቻሞ በግንባር ገጭቶ የመለሳት ኳስ ረመዳን የሱፍ እግር ስር ገብታ ተጫዋቹ በቀጥታ መትቶት የግቡን ብረት ለትማ የተመለሰችሁ ኳስ ስሑል ሽረዎች ለወሰዱት ብልጫ ማሳያ ቢሆንም ግብ ለማስቆጠር አልቻሉም፡፡ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ሲሉ ሳሊፍ ሌላ አጋጣሚ አግኝቶ የመክብብ ሲሳይ ሆናለች ደቡብ ፖሊሶች በአንፃሩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ብርሀኑ በቀለ ያመከናት የመጨረሻ ደቂቃ አጋጣሚም የምታስቆጭ ነበረች፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ በተቃራኒው ደቡብ ፖሊሶች የነበረባቸውን ስህተት አርመው ወደ ሜዳ የገቡበት እና ስሑል ሽረዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያሉ ቢመስሉም በረጃጅሙ ወደ አጥቂዎች በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት የጣሩበት ነበር፡፡ በግራ እና በቀኝ ኮሪደሮች በኩል በመስመር ተጫዋቾቻቸው በይበልጥ በመጠቀም አስበው ወደ ሽረ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ፖሊሶች በተለይ በብሩክ ኤልያስ ፈጣን የሆነ የማጥቃት ሽግግር ተጋጣሚያቸውን ተፈትነዋል፡፡ 48ኛው ደቂቃ ብሩክ በዚሁ የግራ አቅጣጫ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ውስጥ ያሻገራትን ኳስ ኪዳኔ አሰፋ የቀድሞ ክለቡ ላይ ሊያስቆጥር የተቃረበ ይመስል የነበረ ቢሆንም የግቡ ቋሚ ብረት መልሶበታል፡፡ 50ኛው ደቂቃ ላይም ብሩክ በድጋሜ የሽረ ተከላካዮች መቋቋም ባቃታቸው የግራ መስመር ወደ ሳጥን ተጠግቶ ያመቻቸለትን ኳስ ዘላለም ኢሳያስ ከዳዊት አሰፋ ጋር ተገናኝቶ ቢሞክርም ኳሱ የውስጥ ብረቱን ነክቶ ተመልሷል፡፡
53ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ኤልያስ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ለኪዳኔ አሰፋ ሰጥቶት ኪዳኔ ወደ ግብ መትቶ ቋሚ ብረት ሲመልስበት ብርሀኑ በቀለ እግር ስር ገብታ ብርሀኑ ወደ ግብ ሲመታ የሽረው አምበል ዲሚጥሮስ ወልደስላሴ ኳሷን ለማውጣት ሲሞክር በራሱ ግብ ላይ አሳርፎ ቢጫ ለባሾቹን መሪ አድርጓቸዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሙሉዓለም ረጋሳ መትቶት ብረት የመሰለበት አጋጣሚ ደግሞ ሽረዎች ለመሆን የተቃረቡበት ነበር።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ በግራ አቅጣጫ በረመዳን የሱፍ ወደ ግብ በሚላኩ ዕድሎች አቻ ለመሆን ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ስሑል ሽረዎች ተሳክቶላቸው ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ 66ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ሀብታሙ ሸዋለም ሲያሻማ በጨዋታው በርካታ ኳሶች ያመከነው እና በስሑል ሽረ መለያ ተደጋጋሚ ግቦችን እያስቆጠረ የሚገኘው ሳሊፍ ፎፋና የባለሜዳዎቹን ተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሮ አቻ አድርጎቸዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከዕለቱ ዳኞች ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ሲገቡ የነበሩት የስሁል ሽረ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሲያሳዩ የነበሩት ያልተገቡ ባህሪዎችን ተከትሎ የዕለቱ ዋና ዳኛ በምክትል አሰልጣኙ ገብረኪሮስ አማረ ላይ እርምጃ በመውሰድ ከስታድየሙ እንዲወጡ አድርገዋቸዋል፡፡ ደቡብ ፖሊሶች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሄኖክ አየለ እና አናጋው ባደግ የጭማሪ ሰዓት ሙከራ ለማሸነፍ ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨወታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡