በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ኢትዮጵያ በቡሩንዲ 4-1 ተሸንፋለች፡፡ ከጨዋታው በኃላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ስለጨዋታው፣ ሽንፈቱ እና ስለተከላካይ መስመሩ
“በእኛ በኩል ጨዋታው መጥፎ አልነበረም። ነገር ግን ያሉት ወጣት ተጫዋቾች ከበድ ያለ የኢንተርናሽናል ግጥሚያም ይሁን ቡድን በተቃራኒ ሆነው ገጥመው አያውቁም፡፡ ይህ ጨዋታም ለእነሱ ከባድ ነበር፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎች የተሻለ ነገር ለመስራት እና ጥሩ ጨዋታ ለማሳየት እንጥራለን፡፡ የዛሬው ጨዋታ ውጤት ለእኛ መጥፎ ነው፡፡ ሽንፈቱ የእኛ ችግር ነው፡፡
“በግብ ጠባቂ በኩል ይፈጠራሉ ብለን ያሰብነው ነገር የለም። በአጋጣሚ የተፈጠሩብን ነገሮች ናቸው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ አጋጣሚዎችን አግኝተን ነበር፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ወርደን የተሻለ አጋጣሚ መፍጠር አልቻልንም፡፡ የግብ ጠባቂ እና አንዳንድ የመከላከል ስህተቶችም ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ወጣቶች ልምድ ያገኙበታል ብለን ስለመጣን የተሻለ ነገር ይዘው ይመለሳሉ ብለን እናስባለን፡፡
“ምንአልባት ወጣቶች እና ልጆች ስለሆኑ የተጫወቱት ከአንድ ቀን በኃላ ስለሆነ ጉልበታቸውን ጨርሰዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ወጣት እና ልጆች ናቸው። የጨዋታ ልምዳቸው ገና ነው፡፡
“በጉዳት ነው የተከላካይ መስመሩ ላይ ለውጥ ያደረግነው፡፡ ቴዲ (ቴዎድሮስ በቀለ) ተጎድቶ ስለነበረ ነው ተመስገንን ያስገባነው፡፡ ጨዋታው ጥሩም መጥፎም ጎኖች አሉት፡፡ የተሻለ ወደ ግብ እንሄዳለን ፤ ብዙ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። ግን ማጥቃት ብቻውን ውጤት ያመጣል የሚል ሃሳብ የለም፡፡ የመከላከል አደረጃጀት ከሌለ ዋጋ ያስከፍላል። ይህንን ነገር አይተናል፡፡”
ስለቀጣይ ጨዋታ እና አጥቂዎች
“አሁን ላይ ከውድድር አልወጣንም፡፡ ቀጣይ ጨዋታ ማሸነፍ ከቻልን ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማምራት እንችላለን ስለዚህም ለጥሩ ተጋጣሚዎች ተዘጋጅተን ለማሸነፍ እንመጣለን፡፡
“ይህ ሽንፈት ተጫዋቾቻችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ይህ ጨዋታ ለእነሱ ሁለተኛቸው የኢንተርናሽናል ጨዋታ ነው፡፡ ከምድብ ጨዋታው የሆነ ነገር ለማግኘት በአእምሮ ተዘጋጅተን እንመጣለን፡፡
“አጥቂዎቻችን ወጣት እና የኢንተርናሽናል ልምድ የሌላቸው ናቸው፡፡ በተለያየ ግዜ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ሲጫወቱ ግን መልመድ እና የተሻለ መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡”