የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም 22ኛ ሳምንት መሰናዶ እንዲህ ይቀርባል ።
|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ | LINK |
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተፋፋመ ሲሄድ የሶቭየት እግርኳስ የሊግ ውድድር ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ፤ በዘለቄታዊነት የመቀጠል ጋሬጣም ከፊቱ ተደቀነ፡፡ አርካዲዬቭም በ1943 ዳይናሞ ሞስኮን ኋላ ላይ ስያሜው CSKA የተባለው ሲድካ (CdKA)ተቀላቀለ፡፡ በ1952ቱ ኦሊምፒክ ሶቭየት በዩጎዝላቪያ ብሄራዊ ቡድን ለመሸነፏ ሲድካዎች በተጠያቂነት ተፈርጀው በስታሊን ብይን ክለቡ እንዲፈርስ ከመደረጉ በፊት አሰልጣኙ ከቡድኑ ጋር አምስት ጊዜ የሃገሪቱ ሻምፒዮና መሆን ቻለ፡፡
የአርካዲዬቭን እግርኳሳዊ መርሆዎች ይዘው የከረሙት ዳይናሞዎች በ1945 የጦርነቱን ማብቃት ተከትሎ በእንግሊዝ ባደረጉት የወዳጅነት ጉብኝት አጫጭር ቅብብሎች ላይ በተመሰረተውና ፓሶቮችካ /Passovotchkha/ የተሰኘ ስያሜ ባገኘው ማራኪ አጨዋወታቸው ብሪታኒያውያኑን አስደመሙ፡፡ ከቼልሲ ጋር በስታምፎርድ ብሪጅ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ያሳዩት የቡድን አደረጃጀት (Team Build-Up) ግን በፖለቲካዊ ምልከታ ተቃኘባቸው፡፡ በቀደሙት ጊዜያት የብሪታንያ ቡድኖች በደቡብ አሜሪካ ሃገራት በነበራቸው ቆይታ የግጭቶች መንስኤ እየሆኑ የተቸገሩበት አካላዊ ጉሽሚያ የሚያይልበት አጨዋወት እዚህም ችግር እንዳይፈጥር ከፍተኛ ስጋት ጫረ፡፡ በእርግጥ ሁለተኛው ዙር ሊጠናቀቅ በርካታ ወራት ቢቀሩም ቼልሲዎች በደቡብ እንግሊዝ የዲቪዚዮን ውድድር አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኙ ነበር፡፡ ሰማያዊዎቹ ከጨዋታው የ4-4 አቻ ውጤት ለማግኘት ከፍተኛ ትግል ያድርጉ እንጂ ስልጡን የአቀራረብ ዘይቤ (Sophistication of Styles) በማሳየት ረገድ አንጻራዊ ድክመት እንደነበረባቸው ገሃድ ወጣ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ኦስትሪያዊው ሲንድለር ወደኋላ ባፈገፈገ ሚና እንግሊዞችን ችግር ውስጥ እንደጣላቸው፣ ሃንጋሪያዊው ናንዶር ኼጁኩቲም በተመሳሳዩ ስልት ብልጫ እንደወሰደባቸው ሁሉ ኮንስታንቲን ቦስኮቭም በተለምዶ የመሃል አጥቂዎች የሚያዘወትሩት ስፍራ ላይ ለመሰለፍ “እምቢኝ!” ብሎ ቼልሲዎችን ግራ አጋባቸው፡፡
ከዳይናሞዎች አጨዋወት እጅግ አሰደናቂው ነገር ጉልበታቸው ሲሆን ይህን ጠንካራ ጎን የሚጠቀሙበት ብልሃታቸው ደግሞ የተለዩ እንዲሆኑ የረዳቸው ይመስላል፡፡ “ሩሲያዎች በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ንቁዎች ስለነበሩ ፍጹም ልንገዳደራቸው አልቻልንም፡፡” ሲል የዚያኔው የቼልሲ ግራ መስመር ተከላካይ አልበርት ቴናንት ያስታውሳል፡፡ የቀድሞው የሬንጀርሶች አምበል ዴቪ ሜይክልጆን ደግሞ ” የእነርሱ /የዳይናሞዎች/ የቀኝ መስመር አማካይ (Outside-Right) በግራው መስመር እስከሚገኝ እና በተቃራኒ መስመር ያለውም እንዲሁ ተመሳሳዩን ማድረግ እስኪችሉ ድረስ ቦታቸውን ይቀያይራሉ፤ ከዚያ በፊት እግርኳስ በዚህ መልኩ ሲተገበር ያስተዋልኩበትን ሁኔታ አላስታውስም፤ ተጫዋቾቻቸው የሚንቀሳቀሱበትን የሜዳ ክፍል እያጤኑ እነርሱን ለመቆጣጠር መሞከር ልክ ሚስጥራዊ ቦታ የተቀመጠውን ቁልፍ አግኝቶ በውስብስብ ሁኔታ የተቆለፈውን ሳጥን ለመክፈት የሚደረገውን አዕምሮ ፈታኝ የቻይኖች ጨዋታ (Chinese Puzzle) እንደ መጫወት ነበር፡፡ ሶቭየቶቹ በቀላሉ ወዲያ-ወዲህ ይመላለሳሉ፤ ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ አንዳቸው የሌላኛቸው ቦታ ላይ ሲደረቡ አለመታየታቸው ነው፡፡” በማለት <ዴይሊ ሪከርድ> ላይ ጽፏል፡፡
ዳይናሞዎች በብሪታንያ የበላይነት ማሳየታቸውን ቀጠሉ፡፡ ካርዲፍ ላይ የጎል ናዳ አውርደው 10-1 ረቱ፤ አርሰናልንም 4-3 አሸነፉ፤ ከሬንጀርስ ጋር ደግሞ 2-2 አቻ ተለያዩ፡፡ የአጨዋወት ስልታቸው እጅጉን ስሜት በተሞላ መንገድ አድናቆት ይቸረው ገባ፡፡ <ዴይሊ ሜይል> ላይ ጂኦፍሬይ ሲምፕሰን ስለሩሲያውኑ ሲያብራራ ” በጥራት፣ በዘይቤና ስኬታማነት ከእኛ እጅጉን የሚልቅ እግርኳስ ይጫወታሉ፡፡ ከአዝናኝነት እሴት አኳያ አሁን በሊጋችን ለሚካሄዱት ጨዋታዎች ባርኔጣቸውን ወደ ላይ አንስተው እያውለበለቡ አድናቆት የሚቸሩ ሰዎች ለየትኛው አጨዋወት እንደሚጮሁ በጥልቁ ማሰብ ይገባቸዋል፡፡” ይላል፡፡ ከዚያ በኋላ የተነሳው ጥያቄ ‘የሶቭየት እግርኳስ ስልት ከሚከተሉት ፖለቲካዊ ርዕዮተ-ዓለም ጋር መስተጋብር ኖሮት ነበርን?’ የሚል ሆነ፡፡
ምስል፦ ቼልሲ 4-4 ዳይናሞ ሞስኮ፣ የወዳጅነት ጨዋታ፣ ስታምፎርድ ብሪጅ፥ ለንደን፣ ህዳር 13-1945
የሩሲያውያኑ እግርኳስ የቼዝ ጨዋታ ስለመምሰሉ በተደጋጋሚ ተወሳ፤ የዳይናሞዎች አጨዋወት በአብዛኛው ቀድሞ በታቀደባቸውና ዝግጅት በተደረገባቸው እንቅስቃሴዎች (Pre-Planned Moves) ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑም ተወራ፡፡
‘ በመደብ-አልባ ስርዓተ ማኅበር ውስጥ የሚከወነው እግርኳስ (Communist Football) በወገናዊ አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ፣ ተጫዋቾች በቡድን ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው አካላት መሆናቸውን ተገንዝበው እንደ አንድ በመሆን ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ብሪታኒያውኑ በትልቁ ግለሰባዊ አቅምን የማሳየት ትልም ያነገበ አጨዋወትን ይፈቅዳሉ፡፡’ በሚለው ቀላል ዘይቤአዊ አገላለፅ ሊነገር ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ይህን ማሰብ ከእውነታው አያሸሽም፡፡ በቀድሞው ጊዜ በአርሰናል ክለብ ከመሃል አጥቂው ጎን የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside-Forward) በመሆን ያገለገለው አሌክስ ጄምስ <ኒውስ ኦፍ ዘ ወርልድ> ላይ ሲጽፍ ያ የዳይናሞዎች ስኬት በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ የቡድን ስራ ላይ እንደሚመረኮዝ ይጠቅሳል፡፡ ” ዳይናሞዎች ራይክ ካርተር አልያም ስታንሊ ማቲውስ መሳይ በግል ችሎታቸው ነጥረው የወጡ ተጫዋቾች (Individualists) አልነበራቸውም፡፡ እነርሱ በእቅዳቸው መሰረት ይጫወታሉ፤ ልምምዳቸውን በድግግሞሽ እየሰሩ አጨዋወታቸው ላይ ጥራት ይጨምራሉ፤ አልፎአልፎም መጠነኛ ልዩነት እያሳዩ ተገማች ላለመሆን ይጥራሉ፤ በእርግጥ ለአቀራረባቸው መሰናክልና እነርሱን ማሸነፍ የሚያስችል የጨዋታ ስልት (Counter-Method) ይዞ መቅረብ ያን ያህል ከባድ አልነበረም፡፡ በተናጠል ከፍ ያለ ብቃት የሚያሳዩ ተጫዋቾች ስላልነበሯቸው ይህንን እንደ ትልቅ ድክመት መጠቀም ይቻል ነበር፡፡” ብሏል፡፡
ቦስኮቭ፣ ቭዜቮልድ ቦብሮቭ ፣ ቫዚሊ ካርታሴቭ እና የመሳሰሉት ተጫዋቾች በቴክኒካዊ ክህሎት በጥሩ ደረጃ ላይ ነበሩ፡፡ ይህን ማንም ሊክድ አልያም ሊያጣጥል አይቻለውም፡፡ ማን ያውቃል እነዚህ ግለኛ የሶቭየት ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች ችሎታቸውን በተለየ መንገድ ተጠቅመውበትም ይሆናል፡፡
ልክ እንደ ብሪታኒያኑ የህትመት ውጤቶች ሁሉ በዳይናሞ ሞስኮ አርካዲዬቭን የተካው አሰልጣኝ ሚክኻይል ያኩሺንም የቦሪስ አርካዲዬቭ እግርኳስ አቀራረብ ርዕዮታዊ መስመር (Ideological- Line) ላይ ያለውን ህጸጽ አደባባይ የማዋል ጉጉት አደረበት፤ ገቢራዊ ያደርገውም ጀመር፡፡ “በጋራ የመጫወት መርህ የሶቭየት እግርኳስ መዘውር ሆኗል፤ አንድ ተጫዋች ጥሩ ብቃት ማሳየት የሚጠበቅበት በቡድን ስራ ብቻ ሊሆን አይገባም፤ በተናጠልም ከፍተኛ ችሎታን ሊያዳብር ያሻዋል፡፡” ሲል ስለ ስታንሊ ማቲውስ ጥያቄ ቀረበለት፡፡ ” እርሱ ከፍ ያሉ የግል ብቃቶችን ቢይዝም እኛ ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጠው ለህብረት ጨዋታ (Collective Football) ነው፡፡ የተጫዋቾችን የግል ክህሎት የሚመረኮዘው አጨዋወት (Individual Football) ሁሌም ሁለተኛ አጀንዳችን ነው፡፡ የቡድን ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር በማሰብ ለእርሱ ስንል ወደ ተናጠል ብቃት የሚያዘነብል እቅድ አናስቀምጥም፡፡” ሲል ምላሽ ሰጠ፡፡
እንግዲህ ይህን ዓይነቱ አመለካከት በብሪታንያ ስር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ የሚጠይቅ ሒደት በመሆኑ አስገራሚ ኅልዮት ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ምንም እንኳ ቦብ ማጎሪ የ<ፓሶቮችካ> የጨዋታ ዘይቤን በስቶክ ሲቲ ሞክሮ መጠነኛ ስኬት ቢያስመዘግብም እንደ ማቲውስ ያለ ባለክህሎት ተጫዋች ከመያዙ አንጻር ያመጣው ውጤት ሊያስገርም የሚችል አልነበረም፡፡ በዚህም ሳቢያ ከዳይናሞው ጉብኝት የተወሰደው ትምህርት ወደ ተግባር የመለወጥ እጣ አልገጠመውም፡፡ በማዕከላዊው አውሮፓና ደቡብ አሜሪካ የታየውን እድገት ቸል ሲልና ዝቅ አድርጎ ሲመለከት የነበረው የብሪታንያ እግርኳስ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በመጡት ጅምር የለውጥ ዓመታት እንኳ አጠቃላይ የወግ አጥባቂነት መገለጫውን ሊተወው ፍላጎት አላሳየም፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ታላላቅ የመስመር አማካዮች (Wingers) የሃገሪቱን እግርኳስ ባያጥለቀልቁት ኖሮ ምናልባትም ግኝትና ፈጠራን ለሚያበረታታው መንገድ በሩን ገርበብ ያደርግ ነበር፡፡
ግን ግን…. በእንግሊዝ፥ ስታንሊ ማቲውስ፣ ቶም ፊኒ እና ሌን ሻክልተን- በስኮትላንድ ደግሞ ዊሊ ዋድል፣ ጂሚ ዴላይኒ እና ጎርደን ስሚዝን የመሳሰሉ ተጫዋቾች አጠቃላዩ የግል ክህሎታቸው ላይ ልጓም የሚያበጅባቸው የፎርሜሽን ለውጥ ማድረግ ለምን ያስፈልጋል?
የእንግሊዞች የመስመር ጨዋታ (Wing-Play) የከፍታ ዘመን የታየው በማቲውስ ምርጡ ጊዜ በ1953ቱ የማኅበሩ ዋንጫ ፍጻሜ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ያን ዕለት ብላክፑል በተጫዋቹ ቴክኒካዊ ተሰጥኦ፣ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን እያታለለ በሚያልፍበት አብዶዎቹ እና ፍጥነቱ ተበረታትቶ በቦልተን ከ3-1 ከመመራት ተነስቶ 4-3 አሸነፈ፡፡ ያ ድል ሁሌም ታሪካዊ ሆኖ ይኖራል፡፡ ከስድስት ወር በኋላ በዚያው ሜዳ ሃንጋሪ ታሪካዊውን የ6-3 ድል እንግሊዝ ላይ ተጎናጸፈች፡፡ የ<ዴይሊ ሚረር> አርዕስተ-ዜናም የእግርኳስ ፈጣሪዋን ሃገር የመጨረሻ ውድቀት አወጀ፡፡ በመስመር አማካዮች ላይ ጥገኛ ሆኖ ከእግርኳስ ጨዋታ ውበት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እውነትም የምክነት መነሻ ነበር፡፡
ከሁሉ በላይ ሐሳቡን ምጸታዊ የሚያደርገው
ደግሞ የW-M ፎርሜሽን ፈጣሪው ኸርበርት ቻፕማን በመስመሮች ለሚከወን ጨዋታ (Wing-Play) መጠንሰስ እና በመላው ሃገሪቱ መዛመት ተጠያቂ መደረጉ ነው፡፡ በእንግሊዝ እግርኳስ ለግማሽ ምዕተ-ዓመት ያህል በቀዳሚነት እጅግ ጠቃሚ የታክቲክ እድገት ያሳየው የቻፕማን አጨዋወት ሥርዓት ውስጥ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን በብልሃት ማለፍ የሚችሉ የመስመር አማካዮች (Wingers) ነበሩ፡፡ ስለዚህም እነርሱ ገና ከጅምሩ አይነኬ ሆነው ዘለቁ፡፡ በዚህም ሰበብ የቻፕማን ጥንታዊ ግኝት ሌሎች ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ አዳዲስ ፈጠራዎች ላይ ሳንካ ሆነ፡፡ እንደ’ነዚህ ያሉ ተጫዋቾችን የያዙ አሰልጣኞች በተደጋጋሚ ጊዜ ተፈትኖ ወሳኝነቱ የተረጋገጠ የአቀራረብ ዘዴ ላይ ሙጥኝ ቢሎ ምክንያታዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እንዲያም ሆኖ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ባሉት ዓመታት የእንግሊዞች የውጤት ‘ሪከርድ’ ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ ከግንቦት 1947 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል ሽንፈት የሚባል ነገር አልገጠማቸውም፤ በእነዚህ ዓመታት በኢስቶሪል ፖርቹጋልን 10-0 እንዲሁም በቱሪን የወቅቱን የአለም ሻምፒዮን ጣልያንን 4-0 የረቱባቸው አለምአቀፍ ግጥሚያዎችም ተካሂደዋል፡፡ በጊዜው ስኮትላንዶች ወጥ አቋም ባያሳዩም ከጥቅምት 1948 ጀምሮ ያደረጓቸውን ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፈዋል፡፡ የእነዚያ ድንቅ የመስመር አማካዮች ብቃት እንግሊዛውያን ሌሎች ታክቲካዊ አማራጮች የሚሹበት አንጀት እንዳይኖራቸው አድርጎ ሲያስቀር ታዲያ ችግር ተፈጠረ፡፡ የዳይናሞው ጉብኝት ከተደረገ ከስምንት ዓመታት በኋላ ግን በድንገት የብሪታኒያውያኑ ዓይን ተከፈተ፡፡
ይቀጥላል...
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
–Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
–Sunderland: A Club Transformed (2007)
–Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
–The Anatomy of England (2010)
–Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
–The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
–The Anatomy of Liverpool (2013)
–Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
–The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)