“ለአፍሪካ ዋንጫ እንደምናልፍ ተስፋ አደርጋለሁ” ዋሊድ አታ (በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ) 

በቱርክ ገንሰልበርሊጊ እየተጫወተ የሚገኘው ዋሊድ አታ በቱርክ እያሳለፈ ስለሚገኘው የእግርኳስ ህይወቱ ፣ ስለዋሊያዎቹ እና የተለያዩ እግርኳሳዊ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡ እኛም ለአንባቢያን እንዲመች አድርገን አቅርበነዋል፡፡ 

 

ስለገንሰልበርሊጊ

“ቢኬ ሃከንን የለቀኩት ገንሰልበርሊጊ የተሻላ ነገር ስላቀረበልኝ ነው፡፡ የቱርክ ሊግ አውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ ሊጎች አንዱ መሆኑ ወደ ክለቡ እንዳመራ አስገድዶኛል፡፡

አሁን ላይ ያለው የሊግ ውጤታችን ጥሩ አይደለም፡፡ በሊጉ የነበረን የደከመ አጀማመር አሁን ላይ ክለቡ የወራጅ ስጋት እንዲኖርበት አስችሏል፡፡

“ሊጉ ሲጀመር ቋሚ ተሰላፊ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን በክለቡ የአሰልጣኞች መቀያየር ቦታዬን አሳጥቶኛል፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ ያለበቂ ምክንያት ከቡድኑ ቋሚ አሰላለፍ ውጪ አድርጎኛል፡፡ ያንን አከብራለሁ ቢሆንም በቂ የመጫወቻ ግዜ ማግኘት እፈልጋለው፡፡ ስለሆነም ከወከሌ ጋር ተነጋግሬ ከክለቡ የምለያይበትን መንገድ እያጤንኩ ነው፡፡ ከፈረንጆቹ አዲስ አመት በኃላ ወደ አዲስ ክለብ እንደምሄድ ተስፋ አለኝ፡፡ ”

 

ስለቱርክ እግርኳስ እና ሊግ

“ቱርክ በእግርኳስ ያበደ ህዝብ አላት፡፡ በአንካራ በነበረኝ የመጀመሪያ ወራት ቆይታ ባህሉን ፣ ምግቡን እና አከባቢውን መልመድ ቸግሮኝ ነበር፡፡ አሁን በደንብ ተላምጂያለው፡፡ ሊጉ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ አካል ብቃት ላይ የሚያመዝን እግርኳስ ይጫወታሉ፡፡ ሊጉን የሚያደምቁ ስም ያላቸው ዝነኛ ተጫዋቾች መኖራቸው ሲታከልበት ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ተርታ እንደሚመደብ ትረዳለህ፡፡ ”

 

ስለዋሊያዎቹ

“ብሄራዊ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ባሳካቸው ውጤቶች ምክንያት አሁን እየተመዘገበ የሚገኘው ያለው ውጤት አመርቂ አይደለም፡፡ አፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ችለናል፤ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ተቃርበን ነበር፡፡ ህዝቡ ከዚህ የተሻለ ነገር ስለሚጠብቅ ውጤቶች ባሰብናቸው መንገዶች አለመሄዳቸው ያበሳጫል፡፡

“በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሲሸልስ ጋር አቻ መውጣታችን አሳዝኖኛል፡፡ አሁን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ግዴታ ጨዋታዎች ማሸነፍ ይገባናል፡፡ አንደምናልፍ ተስፋ አድርጓለው፡፡ ብሄራዊ ብድኑን ተመልሼ መጥቼ እነደማገለግልም አስባለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ብሄራዊ ቡድኑ ሩዋንዳ ላይ በቻን ውድድር መልካም ውጤት እንዲገጥመው እመኛለሁ”

rabona

በልምምድ ሜዳ ስላስቆጠረው አስገራሚ ራቦና

” ያስቆጠርኩት ራቦና ጎል (እግር አጠላልፎ መምታት) ዓለም ላይ በስፋት ይታያል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ግቧን በሁለተኛ ሙከራዬ ነው ያስቆጠርኳት፡፡ በኢንስተግራም ገፄ ላይ ምስሉ አስቀምቼ ስለነበር ብዙ ሰው ተምልክቶቷል፡፡ ከአሜሪካ እና ብራዚል እንዲሁም ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ብዙ ሰዎች በግቧ ምክንያት መልዕክት ትተውልኛል፡፡ ለኔ በጣም አስገራሚ አጋጣሚ ነበር፡፡ ”

 

ስለየሱፍ ሳላህ

” የሱፍ ጥሩ ጓደኛዬ ነው፡፡ ጥሩ ችሎታ ያለው ተጫዋች ነው፡፡ ስለችሎታው እግርኳስ የሚወደው የኢትዮጵያ ህዝብ መመስከር ይችላል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ቢካተት ደስ ይለኛል ነገር ግን ውሳኔው የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ነው፡፡ ”

 

በተለያዩ ዓለማት ስለሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች

“ለዋሊያዎቹ መጫወት ከጀመርኩ ግዜ አንስቶ ብዙ ተጫዋቾችን የመተዋወቅ ዕድሉ ነበረኝ፡፡ በጀርመን ፣ በስካንዲኒቪያን ሃገራት እና በአሜሪካ የሚጫወቱ ትውልደ ተጫዋቾች አግኝቻለው፡፡ ብዙዎቹ ለኢትዮጵያ መጫወት እንደሚፈልጉ ይነግሩኛል፡፡ እኔ ሳውዲ አረቢያ ነው የተወለድኩት፡፡ እናቴ ከኢትዮጵያ ነች፡፡ ለኔ የተመቻቸው ዕድል ለሁሉም ይመቻቻል የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ነገርግን እግርኳስ ፌድሬሽኑ እነዚህ ተጫዋቾች ኢትዮጵያን የሚጠቅሙበትን ነገር ቢያመቻች ጥሩ ነው፡፡ ከውጪ የሚመጡትን ተጫዋቾች ከሃገር በቀሎች ጋር በማዋሃድ ጠንካራ ብሄራዊ ብድን መገንባት ይቻላል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስን የሚያግዙ መልማዮችን በመቅጠር ትውልደ ኢትዮጵያዊኑ ሃገራቸውን ማገዝ የሚቻሉበትን መንገድ መቀየስ ይቻላል፡፡

 

ስላመለጠው የሳኦ ቶሜ እና ፕሪስፔው ጨዋታ

” ጉዳዩ በጣም የሚሳዝን ነው፡፡ ፌድሬሽኑ ያደረገው ነገር ከእግርኳስ አግባብ ልክ አይደለም፡፡ ጉልቤቴን መታየት ስለነበረብኝ ስቶኮልም ወዳለው የግል ሃኪሜ ሂጄ ነበር፡፡ የፌድሬሽኑ ሰዎች የአውሮፕላን ትኬት ልከውልኝ ከስቶኮልም ወደ ሳኦ ቶሜ እንድመጣ ተስማምተን ነበር፡፡ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ብዙ ግዜ የስልክ ጥሪዎችን አድርጌ ነበር:: ግን የሚረዳኝ ሰው አላገኘውም፡፡ ለሁለተኛው ጨዋታ እደርሳለው ብዬ ጠብቄ ነበር ግን አሁንም ከፌድሬሽኑ የመጣ ነገር ስላስነበረ ጨዋታው አምልጦኛል፡፡ በዚህ የተነሳ ክለቤ ለምን ወደ ብሄራዊ ቡድኔ እንዳልሄድኩ ጥያቄ አቅርቦልኝ ፌድሬሽኑን እስከመከላከል ደርሻለው፡፡ ለወደፊቱ እንደዚህ ዓይነቱ ችግር እንደማይደገም ተስፋ አለኝ፡፡ ”

 

ስለወደፊት እቅዱ

“በአፍሪካ ዋንጫ መጫወት እፈልጋለው፡፡ አውቃለው ያንን ባሳካ እናቴ በጣም እንደምትኮራ፡፡ እግርኳስ ካቆምኩ ባኃላ ባለኝ ልምድ የኢትዮጵያን እግርኳስ ብረዳ ደስ ይለኛል፡፡”

ያጋሩ