የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ፍፃሜ በበዓምላክ ተሰማ ዳኝነት ይመራል

የ2018/19 ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከነገ በስቲያ ፍፃሜውን ሲያገኝ በግብፁ ዛማሌክ እና የሞሮኮው በርካኔ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ በዓምላክ ተሰማ እንዲመራ በካፍ ተመድቧል።

ከ5 ቀናት በፊት በሞሮኮ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ባለሜዳው አር ኤስ በርካኔ በመጨረሻ ደቂቃ ኮጆ ላባ ባስቆጠረው ጎል ማሸነፍ የቻለ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ በአሌክሳንድሪያው ቦርግ አል አረብ ስታድየም እሁድ ምሽት ይካሄዳል። ይህን ጨዋታም ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በመሐል ዳኝነት ይመራዋል።

ደቡብ አፍሪካዊው ዛኪይ ሲዎሊ እና የሴኔጋሉ አልሀጂ ማሊክ በረዳትነት ሲመሩ ቱኒዚያዊው ሳዶክ ሴልሚ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል። በሞሮኮ የተካሄደውን የመጀመርያው ጨዋታ የመራው ጃኒ ሲክዌዜ ደግሞ ከሱዳናዊው ዋሊድ አህመድ እና ሴኔጋላዊው ጋብሬል ካማራ ጋር በመሆን የVAR ዳኝነቱን ይመራል።

በዓምላክ ሁለት ተከታታይ የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜዎችን እና ከወራት በፊት በዶሀ የተከናወነው የካፍ ሱፐር ካፕ ጨዋታን በመምራት ታላቅ ዳኝነቱን ያሳየ ሲሆን አሁን ደግሞ ወሳኙን የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በመጪው ሰኔ በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከሚሳተፉ ዳኞችም አንዱ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡