ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ፋሲል ከነማ

ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ሶዶ ላይ የሚደረገው እና ሦስቱን ወንድማማቾች የሚያገናኘው ሌላው የነገ ተጠባቂ ጨዋታ ነው።

በሰንጠረዡ ላይ እና ታች ባሉት ትንቅንቆች ውስጥ የሚገኙት ድቻ እና ፋሲል በውድድሩ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ሆነው ነገ እርስ በርስ ይገናኛሉ። ከዚህ ባለፈም ጨዋታው የፋሲሉን ሽመክት ጉግሳን ወላይታ ድቻ ከሚገኙት ወንድሞቹ አንተነህ ጉግሳ እና ቸርነት ጉግሳ ጋር የሚያገናኝ መሆኑ ሦስቱም የመሰለፍ ዕድል ካገኙ አጋጣሚውን የተለየ ያደርገዋል። ከደደቢት ካገኟቸው ሦስት የፎርፌ ነጥቦች በኋላ ከወልዋሎ አንድ ነጥብ ይዘው የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች ከ20ኛው ሳምንት በኋላ የራቃቸውን ድል በሊጉ መሪዎች ላይ አሳክተው አፋፍ ላይ ከሚገኙበት ወራጅ ቀጠና ለመራቅ ይጫወታሉ። ሳምንት በግብ ተንበሽብሸው ወደ ሊጉ አናት የመጡት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ስድስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተው ወደ ዋንጫዉ መቅረብ አላማቸው ነው።

ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መምጣት በኋል ታይቶባቸው የነበረው መነቃቃት እየቀነሰ የመጣው ወላይታ ድቻዎች ካለባቸው ስጋት ነፃ ለመሆን የሚያስችሏቸውን ነጥቦች ለማሳካት ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይገመታል። ከሁሉም በላይ ተጋጣሚያቸው ካለበት ድንቅ አቋም እና ከፍ ያለ የማሸነፍ ስነ ልቡና አንፃር ራሳቸውን በአዕምሮው ረገድ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ለኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቦታ ያለው ቡድኑ የፋሲልን ጠንካራ የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ የቁጥር ብልጫን በመውሰድ ለመግታት አምስት አማካዮችን ሊጠቀም እንደሚችል ሲገመት እንደተለመደው ሁለት አጥቂዎችን ካሰለፈም አንደኛው ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ መንቀሳቀሱ የሚቀር አይመስልም። ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብ ያላቸው የጦና ንቦቹ በአዲሱ የተስፋዬ አለባቸው እና በረከት ወልዴ የተከላካይ አማካይ ጥምረት በተሰጥኦ የተሞላው የፋሲልን የማጥቃት አማካዮች እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያሳልፏችው ውሳኔዎችም ከጨዋታው የሚጠብቁትን ውጤት የመወሰኑ ጉዳይ የሰፋ ነው።

አዲሶቹ የሊጉ መሪዎች አሁን ላይ ቡድናቸው በሁሉም መልኩ የተዋጣለት ሆኗል። ተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን ሲያሸንፉ 18 ግቦችን ማስቆጠራቸው ብቻ ሳይሆን ያስተናገዷቸው ግቦች ሁለት ብቻ መሆናቸውን ማስተዋል ይህን ለማለት በቂ ነው። ቡድኑ ከሚከተለው በኳስ ቁጥጥር ላይ ከተመሰረተ አቀራረብ አንፃር በነገው ጨዋታ በሜዳው ሁኔታ ሊፈተን የሚችልበት ዕድል ቢኖርም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን የማሳካት ዕድሉ ሰፊ ነው። የኤፍሬም ፣ በዛብህ እና ሱራፌል የአማካይ ክፍል ጥምረት ሲታይም ሦስቱም ቡድኑ ወደ ፊት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ አስተዋፅዖ የማድረግ የአጨዋወት ባህሪን መላበሳቸው ከመስመር አጥቂዎቹ ታታሪነት ጋር ተደምሮ የፋሲልን የማጥቃት ኃይል አስፈሪ ያደርገዋል። አፄዎቹ የተረጋጋ የመጀመሪያ አሰላለፍ ምርጫን ይዘው ድሎችን እያሳኩ መምጣታቸውም ነገም ተመሳሳይ መንገድን እንደሚመርጡ የሚጠቁም ነው። ሆኖም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጨዋታው ከሜዳ ውጪ እንደመደረጉ ጉዳት ላይ በሚገኘው ሀብታሙ ተከስተ ቦታ የመከላከል ባህሪ ያለው አማካይ ሊጠቀሙም ይችላሉ። ከወቅታዊው ውጤት አንፃር ፤ በአጠቃላይ ቡድኑ በተለይ ደግሞ ጅማ ላይ አራት ግቦችን ያስቆጠረው ሙጂብ ቃሲም የሚገኙበት የአዕምሮ ጥንካሬም ፋሲሎች በሊጉ መሪነት ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ውጤት ከሶዶ ይዘው ለመመለስ ትልቁ መተማመኛቸው ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች አምስት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ሦስቴ ድቻ ደግሞ ሁለት ጊዜ መሸናነፍ ችለዋል። እስካሁን የአቻ ውጤት ባልተመዘገቡባቸው እነዚህ ጨዋታዎች ሁለቱም አምስት አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

– ሶዶ ላይ አስር ጨዋታዎችን ያደረገው ወላይታ ድቻ አምስቱን በድል አራቱን ደግሞ በአቻ ውጤቶች ሲያጠናቅቅ ለመጨረሻ ጊዜ ባስተናገደው መከላከያ እጅ የደረሰበት ሽንፈት ብቸኛው ነጥብ ያልያዘበት ጨዋታው ሆኖ አልፏል።

– ፋሲሎች ከጎንደር ወጥተው ባደረጓቸው 12 ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ አራት ጊዜ ድል አድርገው በሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፈዋል። የመጨረሻዎቹ አምስት ጉዞዎቻቸውም ከሽንፈት የፀዱ ነበሩ።

ዳኛ

– 11 ጨዋታዎችን ዳኝቶ 47 የቢጫ ካርዶችን እንዲሁም አራት ቀጥታ ቀይ ካርዶችን የመዘዘው እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ ከዚህ ቀደም ፋሲልን ከጅማ ጋር ያጫወተ ሲሆን ወላይታ ድቻን ለመጀመሪያ ጊዜ ይዳኛል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-2-3-1)

መኳንንት አሸናፊ

እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ተክሉ ታፈሰ – ሄኖክ አርፌጮ

በረከት ወልዴ – ተስፋዬ አለባቸው

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ቸርነት ጉግሳ

ባዬ ገዛኸኝ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ኤፍሬም አለሙ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡