ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የዋንጫ ጉዞውን ያሳመረበትን ድል አስመዝግቧል

ሀዋሳ ላይ ሁለቱን የአንድ ከተማ ክለቦች ያገናኘው የሲዳማ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ ጨዋታ በሲዳማ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ ከተጠቀመበት አሰላለፍ ውስጥ ዳዊት ተፈራን በወንድሜነህ ዓይናለም እንዲሁም መሀመድ ናስርን በይገዙ ቦጋለ ሲተካ በሜዳቸው ከስሑል ሽረ ነጥብ የተጋሩት ደቡብ ፖሊሶች በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ አበባው ቡታቆ እና ብርሀኑ በቀለን በዘነበ ከድር እና በረከት ይስሀቅ ለውጠዋል።

ጨዋታው ከ17 ዓመት በፊት ህይወታቸውን ላጡ የሲዳማ ወጣቶች የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኃላ ለ15 ያህል ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረ ነበር፡፡ ሊዘገይ የቻለበትም ምክንያት የዕለቱ ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በስታድየሙ ቅጥር ግቢ ያለአግባብ የገቡ ሰዎች ይውጡ በማለታቸው የተነሳ ነበር ፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ረጃጅም ኳሶችን መጠቀምን ምርጫቸው እንዳደረጉ ፍንትው አድርጎ ያሳየን ነበር። እጅግ ቀዝቃዛ እና ሳቢ ያልሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ባየንበት በዚሁ አጋማሽ ደቡብ ፖሊሶች በረጅሙ ኳሶችን ወደ ሄኖክ አየለ ማሻገር ላይ ትኩረት ሲያደርጉ የሲዳማዎች ምርጫ ደግሞ የቀኝ እና ግራ ኮሪደሩ ላይ የአዲስ እና ሀብታሙን እንቅስቃሴ ያማከለ ነበር። የጨዋታው ቀዳሚ ሙከራ ሄኖክ አየለ ከመክብብ ደገፉ በደረሰው ረጅም ኳስ ከግራው የሳጥን ጠርዝ ላይ ሞክሮ በግቡ አግዳሚ በኩል የወጣበት ኳስ ሆኗል። ሲዳማዎችም ዮሴፍ ዮሀንስ ከርቀት ሞክሮ ግብ ጠባቂው መክብብ በያዘበት ጠንካራ ሙከራ ምላሽ ሰጥተዋል።

ፖሊሶች በሂደት ብሩክ ኤልያስን በመስመር ወደ ፊት ካስጠጉ በኃላ ይበልጥ ተጭነው በመጫወት ተጋላጭ የነበረው የሲዳማን የኋላ ክፍል ፈትነዋል። 13ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አየለ ከቅብብል ስህተት ከፈቱዲን እግር ስር ነጥቆ ወደ ግብ እየነዳ በመግባት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በሁለት የመከላከል ባህሪ ያላቸውን አማካዮችን ሲጠቀሙ የነበሩት ሲዳማዎች የአጥቂ አማካያቸው ወንድሜነህ ዓይናለም ጉዳት ገጥሞት ወደ ሆስፒታል በማምራቱ ዳዊት ተፈራን ካስገቡ በኋላ የተረጋጋ የአጨዋወት መንገድን ሊከተሉ ችለዋል፡፡ 18ኛው ደቂቃ ላይም ሀብታሙ ከቀኝ መስመር በጥሩ ሁኔታ የሰጠውን ኳስ አዲስ ግደይ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ሲዳማ ቡናዎች በቀላሉ የቢጫ ለባሾቹን የመከላከል መንገድ አስከፍቶ ለመግባት በመቸገራቸው ከሳጥን ውጪ በሚገኙ አጋጣሚዎች አማራጮችን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ የደቡብ ፖሊሱ ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ ጥረት ግን ሙከራዎቹን ግብ ከመሆን አድኗቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ 24ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ከሀብታሙ በመቀበል ከርቀት የሞከረው ኳስ የሚጠቀስ ነው።

የዕረፍት መውጫ ደቂቃዎች ሲቃረቡ በሙከራ ረገድ ተሽለው የታዩት ቢጫ ለባሾቹ በኩል በ28ኛው ደቂቃ ዘላለም ኢሳያስ በቀኝ አቅጣጫ ያሻገራትን ኳስ የሲዳማው ተከላካይ ፈቱዲን ለማውጣት ሲንሸራተት በራሱ ላይ ለማስቆጠር የተቃረበ ቢመሰልም ኳሷ ብረት ገጭታለች፡፡ ፖሊሶች በዘላለም ኢሳያስ ኢላማዋን የጠበቀች የርቀት ሙከራን ካደረጉ ሁለት ደቂቃ በኋላ ግን ብሩክ ኤልያስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ መሬት ለመሬት ወደ ግብ የላካትን ኳስ ፈቱዲን ጀማል ተንሸራቶ ለመውጣት ሲሞክር ከጀርባው በነበረው ሄኖክ አየለ አማካይነት ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በ44ኛው ደቂቃም ሄኖክ አየለ በረከት ይስሀቅ ከተከላካዩ ዮናታን እግር ስር ነጥቆ እየገፋ በመሄድ የሰጠው ኳስ በፍቅሩ ተመልሶበታል፡፡

አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ስህተቱ በርከት ያሉበት ፈቱዲንን ቀይረው በማስወጣት የአማካይ ክፍሉን ለማብዛት በማሰብ አበባየው ዮሃንስን አስገብተዋል፡፡ በጭማሪ ደቂቃም አበባየው ከመሀል ሜዳ ትንሽ ጠጋ ብሎ ከርቀት የመታው ኳስ መክብብ ለመያዝ ሲሞክር የጣለው ዝናብ አቅጣጫውን አስቶት በተቆጠረች ድንቅ ግብ በ1-1 ውጤት ወደ ዕረፍት አምርተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የገቡት ሲዳማዎች መሀል ሜዳ ላይ የነበረባቸውን ክፍተት በዳዊት ተፈራ አስደናቂ እንቅስቃሴ በመቅረፍ እንዲሁም በአዲስ እና ሀብታሙ ወደ መሀል የሚገባ ማጥቃት በመታገዝ የ4-3-3 የጨዋታ መንገዳቸውን በደንብ ያሳዩ ቢሆንም ፖሊሶች ብሩክን ወደ ማጥቃት ዞኑ ስበው በመጫወት ከማጥቃት አልቦዘኑም። 50ኛው ደቂቃ ዳዊት ከማዕዘን ሲያሻማ ሰንደይ በግንባር ገጭቶ መክብብ እንደምንም አውጥቶበታል፡፡ 54ኛው ደቂቃ ላይም ዳዊት ከሀብታሙ እና ዮናታን ጥሩ ቅብብል መነሻነት ያደረገውን ሙከራ አስደናቂ የነበረው ግብ ጠባቂው መክብብ በድጋሜ አድኖበታል፡፡ ያም ቢሆን ቀጣዩን ግብ ያስቆጠሩት ፖሊሶች ሆነዋል። በረከት ይስሀቅ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ ብስለቱን በሚገባ በመጠቀም ሳጥን ውጥ ከገባ በኋላ ግቧን ያስቆጠረውም ሄኖክ አየለ ነበር።

ልክ ግቧ ስትቆጠር ከጨዋታ ውጪ ነች በማለት ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን የደቡብ ፖሊሱ ቡድን መሪ ማቲዮስ ዲዳሞ ከደጋፊዎች ጋር ግጭት ውስጥ በመግባቱ ምክንያት ደጋፊው የፕላስቲክ ኮዳዎችን ወደ ሜዳ በመወርወሩ ጨዋታው ለ21 ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዷል። የሲዳማ ቡና አመራሮች እና ተጫዋቾች ደጋፊው እንዲረጋጋ ካደረጉ በኃላ በድጋሚ እንደጀመረ ጫን ብለው መጫወት የቻሉት ሲዳማዎች አቻ ለመሆን ሁለት ደቂቃ ብቻ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ሀብታሙ ገዛኸኝ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘቸሁን ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ ከሳጥኑ ግራ አቅጣጫ በመምታት አስቆጥሮ 2-2 አድርጓቸዋል፡፡በመቀጠልም 71ኛው ደቂቃ ላይ ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ዳዊት ተፈራ መሀል ለመሀል ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ጫላ ተሺታ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን ወደ 3-2 መሪነት አሳድጓል፡፡ መበለጣቸው የገባቸው ፖሊሶች የመልሶ ማጥቃትን ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ አማካዩ ዘላለም ኢሳያስ በግሩም ሁኔታ ሰጥቶት ሄኖክ ግልፅ የማግባት አጋጣሚን አግኝቶ መጠቀም ሳይችል የቀረበት አጋጣሚም ቡድኑን አቻ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር። ግብ ካገቡ በኃላ መቀዛቀዝ ቢታይባቸውም ወደፊት ተስቦ ለመጫወት ያልተቸገሩት ሲዳማዎች 90ኛው ደቂቃ ላይ የማሳረጊያዋን ግብ አግኝተዋል፡፡ ዳዊት ተፈራ እና ሀብታሙ ማራኪ አንድ ሁለት ቅብብልን ካደረጉ በኃላ ሀብታሙ ገዛኸኝ በቀድሞው ክለቡ ላይ አስቆጥሯል። ሀብታሙ ግብ ካገባ በኃላ ለቀድሞው ክለቡ ሲል ደስታውን ሳይገልፅም ቀርቷል፡፡ጨዋታውም በ 4-2 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡