በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘውን የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ ለውጥ እያሳዩ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሱት ስሑል ሽረዎች በሜዳቸው ያላቸው ጥሩ የማሸነፍ ክብረ ወሰን ላለመውረድ ለሚያደርጉት ትግል የሚያግዛቸው ነው። በዋነኝነት በመስመር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት ያላቸው ሽረዎች በመጀመርያው ዙር የነበራቸው የመከላከል ችግር በመጠኑ መቅረፋቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ቢሆንም አሰልጣኙ አሁንም በጉዳት በርካታ ተጫዋቾቹ ማጣቱ ግን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ይሰጋል። ቡድኑ ነገም እንደባለፉት ጨዋታዎች ተለጥጠው ከጥልቀት በሚነሱ የአጥቂ አማካዮች እና በማጥቃቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባላቸው የመስመር በአጥቂዎቹ መሰረት ያደረገ የመስመር ማጥቃት ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል። ስሑል ሽረዎች ሰንደይ ሮትሚ ፣ ዮናስ ግርማይ እና አርዓዶም ገብረህይወትን በጉዳት አያስልፉም።
የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኃላ መጠነኛ መነቃቃት ያሳዩት መከላከያዎች የነገው ጨዋታ ማሸነፍ ደረጃቸውን ለማሻሻል ስለሚረዳቸው በዋነኝነት ማሸነፍን አልመው እንደሚገቡ ዕሙን ነው። በአመዛኙ የኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን የሚከተሉት መከላከያዎች ነገም ከዚህ አጨዋወታቸው የወጣ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ሁለቱ አማካዮቻቸው አማኑኤል ተሾመ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ለተከላካዮች ቀርበው ሽፋን ሰጥተው እንዲጫወቱ ካደረጉ በኃላ ጥሩ የመከላከል ቅርፅ የያዙት ጦሮቹ ጥሩ የግብ ማግባት ክብረ ወሰን ካላቸው የስሑል ሽረ አጥቂዎች የሚጠብቃቸው ፈተና በጨዋታው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በፈጣሪ አማካዮች እና ከመስመር በሚነሳው ፍሬው ሰለሞን ለማጥቃት የሚሞክሩት መከላከያዎች መሃል ለመሃል ከሚደረጉ ጥቃቶች በበለጠ የስሑል ሽረ የመስመር ተከላካዮች ለማጥቃት ትተውት የሚሄዱት ቦታ ለመጠቀም የመስመር ጥቃቶች ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ይገመታል። መከላከያዎች ሽመልስ ተገኝን በአምስት ቢጫ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው ምንይሉ ወንድሙን ሳይዙ ወደ ሽረ እንዳስላሴ አምርተዋል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱን ክለቦች ያገናኘው የአዲስ አበባ ስታድየሙ የረፋድ 04፡00 ጨዋታ 2-2 በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።
– ስሑል ሽረዎች በሜዳቸው በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ አንዴ የተሸነፉ ሲሆን በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ድል ቀንቷቸዋል።
– ከሜዳው ውጪ 11 ጨዋታዎችን ያከናወነው መከላከያ ሦስቱን በድል ሲወጣ በአራቱ ነጥብ ተጋርቶ ሲመለስ አራት ሽንፈቶች ገጥመውታል።
ዳኛ
– ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይመራዋል። አርቢትሩ በእስካሁኖቹ 12 ጨዋታዎች 55 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲያሳይ አንድ ጊዜ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሦስት ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተጫዋቾችን ለሜዳ አሰናብቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ዳዊት አሰፋ
ዓብዱሰላም አማን – ክብሮም ብርሃነ – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ረመዳን ናስር
ብሩክ ተሾመ – ደሳለኝ ደባሽ
ቢስማርክ አፖንግ – ያስር ሙገርዋ – ቢስማርክ አፒያ
ሳሊፉ ፎፋና
መከላከያ (4-2-3-1)
አቤል ማሞ
ሙሉቀን ደሳለኝ – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ታፈሰ ሰረካ
አማኑኤል ተሾመ – ቴዎድሮስ ታፈሰ
ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ፍሬው ሰለሞን
ፍቃዱ ዓለሙ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡