ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ26ኛ ሳምንት የዕሁድ ጨዋታዎች

ባህር ዳር ፣ አዳማ እና አዲስ አበባ ላይ በሚደረጉትን የነገ ሦስት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

6ኛ እና 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀነጡት ባህር ዳር እና ወልዋሎ ነገ 09፡00 በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም ይገነኛሉ። ከጨዋታው የሚገኙት ነጥቦች በቅርብ ሳምንታት እምብዛም ውጤት ያልቀናቸውን ሁለቱን ተጋጣሚዎች የፊተኞቹ አምስት ክለቦች ጋር ባያደርሷቸውም ልዩነታቸውን የማጥበብ ዕድል ግን ይሰጧቸዋል። 

ከመጨረሽ አምስት ጨዋታዎቻቸው በአንዱ ብቻ ድል የቀናቸው ባህር ዳሮች አሁንም በርካታ ተጫዋቾቻቸውን ግልጋሎት አያገኙም። በቋሚነት ቡድኑን ሲያገለግሉ የነበሩት ወሰኑ ዓሊ እና አሌክስ አሙዙ አምስት ቢጫ በማየታቸው ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። ከሁለቱ ወሳኝ ተጨዋቾች በተጨማሪም ዜናው ፈረደ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ፣ ሳላምላክ ተገኝ ፣ ተስፋሁን ሸጋው ፣ ሄኖክ አቻምየለህ ፣ ዳግማዊ ሙሉጌታ እና ማራኪ ወርቁ ጉዳት በማስተናገዳቸው የነገው ጨዋታ ያልፋቸዋል። መቐለ ላይ ደደቢትን ከረቱ በኋላ ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ወልዋሎዎች ግን ያለምንም ጉዳት እና ቅጣት ዜና ወደ ጨዋታው ያመራሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ በሪችሞንድ ኦዶንጎ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ወልዋሎ 1-0 ያሸነፈበት ነበር።

– በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ያለሽንፈት እየተጓዙ የሚገኙት ባህር ዳሮች ሰባት የድል እና አምስት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።
   

– በአስር አጋጣሚዎች ከትግራይ ስታድየም ውጪ የተጫወቱት ወልዋሎዎች አምስት ጊዜ በሽንፈት ሲመለሱ ሁለት የአቻ እና ሦስት የድል ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል።

   
ዳኛ

– ጨዋታውን ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።  አርቢትሩ እስካሁን በመራቸው ሰባት ጨዋታዎች 18 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሔሱ

ግርማ ዲሳሳ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ሚኪያስ ዳኛቸው – ደረጄ መንግስቱ – ኤልያስ አህመድ

ፍቃዱ ወርቁ – ጃኮ አራፋት – ልደቱ ለማ

ወልዋሎ ዓ /ዩ (4-4-2)

ዓብዱልአዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – በረከት ተሰማ – ደስታ ደሙ – ብርሃኑ ቦጋለ
         

አማኑኤል ጎበና – ብርሃኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ – ኤፍሬም አሻሞ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ራችሞንድ አዶንጎ         

                                                                                   
አዳማ ከተማ ከ ደደቢት

ምንም እንኳን ለከፋ ስጋት ባይጋለጥም ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ 12ኛ ደረጃ ላይ የተገኘው አዳማ ከተማ መውረዱን ለማረጋገጥ የተቃረበው ደደቢትን የሚገጥምበት ጨዋታ ሌላኛው የነገ መርሐ ግብር ነው። አዳማ ከተማ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለመጠጋት በሚያደርገው በዚህ ጨዋታ ቅጣት ጥሎባቸው የነበሩት በረከት ደስታ እና ከነዓን ማርክነህን ወደ ሜዳ እንደሚመልስ ሲጠበቅ ዓመቱን በጉዳት ያሳለፈው አንዳርጋቸው ይላቅ እና ዳዋ ሆቴሳ ግን ነገም ጨዋታው ያመልጣቸዋል። የመጨረሻ ዕድሉን በሚሞክረው ደደቢት በኩል ደግሞ ኩማ ደምሴ እና እንዳለ ከበደ በጉዳት መድሃኔ ብርሃኔ ደግሞ በቅጣት ጨዋታው ያልፋቸዋል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ደደቢት እና አዳማ ከተማ በሊጉ ከተገናኙባቸው 17 ጨዋታዎች ውስጥ 32 ግቦች ያስቆጠረው ደደቢት 8 ጨዋታዎችን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 5 ጊዜ አሸንፎ 16 ግቦችን አስቆጥሯል። ቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። 

– አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ስድስት ጨዋታዎችን በድል መወጣት ችሏል። 

– ከመቐለ ውጪ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት በመጨረሻው የአዲስ አበባ ጉዞው መከላከያ ከመርታቱ በቀር ሌላ ነጥብ ማግኘት አልቻለም።

ዳኛ

– ጨዋታው በኄኖክ አክሊሉ የመሀል ዳኝነት የሚመራ ይሆናል። በጥቂት ጨዋታዎች በርካታ ጠንካራ ውሳኔዎች ያሳለፈው አርቢትሩ እስካሁን ስድስት ጨዋታዎችን የዳኘ ሲሆን ስድስት የቢጫ እና ሁለት የቀይ ካርዶችን ሲመዝ አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶችንም ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1) 

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ተስፋዬ በቀለ

ብሩክ ቃልቦሬ – ኢስኤል ሳንጋሪ

አዲስ ህንፃ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ቡልቻ ሹራ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውኪል

አብዱላዚዝ ዳውድ – ኃይሉ ገብረየሱስ – አንቶንዮ አቡዋላ – ሄኖክ መርሹ

የአብስራ ተስፋዬ – ኤፍሬም ጌታቸው

አቤል እንዳለ – አለምአንተ ካሳ – ፉሰይኒ ኑሁ

መድሃኔ ታደሰ             


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ

26ኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ነገ አስር ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማን በማገናኘት ይጠናቀቃል። ከላይ ወዳሉት ሦስት ክለቦች ለመቅረብ ጨዋታውን የሚያደርጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሳላዲን ሰዒድ ፣ ጌታነህ ከበደ እና መሀሪ መና በተጨማሪ በኃይሉ አሰፋ እና አቡበከር ሳኒን በጉዳት ያጣሉ። ፈረሰኞቹ የዛሬን ውጤት ተከትሎ 49 ነጥብ ላይ ከደረሱት ቡድኖች ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ስድስት ቀንሰው ቀሪዎቹ ጨዋታዎች ላይ ጥቂት ተስፋን ለማድረግ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል ። በአንፃሩ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ሆኖ በተከታታይ ዓመታት ከገጠሙት የመውረድ ስጋቶች የራቀው ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ደረጃዎችን ለማሻሻል በማለም ወደ ጨዋታው ይገባል። ቡድኑ ከራምኬል ሎክ እና ኢታሙና ኬይሙኒ ጉዳት በተጨማሪ ዘነበ ከበደ ፍቃድ ላይ በመሆኑ ምክንያት የሚያጣው ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ድሬዳዋ ከተማ 3 አሸንፏል፡፡ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጊዮርጊስ 26 ጎሎችን ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 12 ጎሎች አሉት።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 ጨዋታዎችን በሜዳው አድርጎ ሰባቱን ሲያሸንፍ ስድስት የአቻ እና አንድ የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል።

– ከ12 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሁለቴ ድል የቀናቸው ድሬዳዋ ከተማዎች አምስት ጊዜ አንድ ነጥብ ይዘው ሲመለሱ አምስቴ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።

ዳኛ

– ጨዋታውን የሚመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ እስካሁን 12 ጨዋታዎችን ዳኝቷል። በጨዋታዎቹ 45 የቢጫ ካርዶችን መዞ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ኢሱፍ ቡርሀና – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

                  
ናትናኤል ዘለቀ – ሙሉዓለም መስፍን – ታደለ መንገሻ

አቤል ያለው – ሪቻርድ አርተር – አሜ መሀመድ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ሳሙኤል ዮሀንስ

 ፍሬድ ሙሸንዲ – ሚኪያስ ግርማ 

ኤርሚያስ ኃይሉ – ምንያህል ተሾመ – ረመዳን ናስር 

ሀብታሙ ወልዴ                 

                       


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡