የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 4-2 ደቡብ ፖሊስ


በ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለዋንጫ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ያሉትን ሲዳማ ቡናን እና ደቡብ ፖሊስን አገናኝቶ በሲዳማ ቡና 4-2 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኃላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

ስህተቶቻቸውን በመጠቀም ነው ግብ ያስቆጠርነው” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለ ጨዋታው

የመጀመሪያው አጋማሽ የመከላከል መንገዳችን ጥሩ አልነበረም፤ ወደ ፊትም አንፈጥንም። በመልሶ ማጥቃት እነሱ በተደጋጋሚም ይመጡብን ነበር። ፈቱዲን ሜዳ ልንገባ አካባቢ የሆድ ህመም ገጠመው። አሟሙቀን ሜዳ ልንገባ ስንል ነበር የህመም ስሜት የገጠመው። ይህ ደግሞ ሜዳ ላይ ተንፀባርቋል። ስለዚህ መከላከላችን ላይ መዘናጋቶት ነበሩ። ከእረፍት በፊት ቡድኔ ጥሩ አልነበረም፤ተዘናግተው በመልሶ ማጥቃት ይመጡ ስለነበር ነው ይህ የሆነው። ከእረፍት በኃላ ግን ልጆችን ቅያሪ አድርገን ጨዋታውን ለመቆጣጠር ችለናል፡፡ የነሱ አጨዋወት አስገድዶን ቅያሪ ልናደርግ ችለናል። በተቀያሪዎች ግን ግብ አስቆጥረናል፡፡ ትንሽ ተፈትነን ነበር፡፡ ሁለተኛውን ጎል ካገባን በኃላ በይበልጥ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎሎ በመድረስ ስህተቶቻቸውን በመጠቀም ነው ግብ ያስቆጠርነው ፡፡

ስለ ዳዊት ተፈራ እንቅስቃሴ

ዳዊት እና ወንድሜነህ የአጥቂ አማካዮች ናቸው። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስንጫወት ወንድሜነህ ዓይናለም በሰጣቸው ኳሶች ነው አሸንፈን የወጣነው። .ያን ለማስቀጥል ስለፈለኩም ነበር ቅድሚያውን ለወንድሜነህ ዛሬም የሰጠሁት። ወንድሜነህ ዛሬ ተጎድቶ እስኪወጣ ድረስ ጥሩ ነበር፡፡ ከዛ በኃላ ዳዊትን መቀየር ከቻልን በኃላ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ብልጫውን ወስደን ተጫውተን ቡድኔ አሸናፊ ሆኗልና ቀይረነው አስገብተንም ተጠቃሚ ሆነናል፡፡

ስለ ዋንጫ ጉዞው

ወራጅ ላይ ያሉ ቡድኖች እንደዛሬው ሊፈትኑን ይችላሉ። ግን በስነ-ልቦናው በየትኛውም መንገድ ተዘጋጅተን ቀጣይ ያለውን ጨዋታ ከዚህ በፊትም እንደምለው ከፊት ያለንን ጨዋታ ነው የምንመለከተው። አሁን ለመከላከያ ነው ትኩረታችን፤ መከላከያን አሸነፈን የዋንጫ ጉዟችንን መመልከት ነው የኛ ሀሳብ። ትኩረታችን ስለዋንጫው ሳይሆን የመከላከያ ጨዋታ ነው።

“ዛሬ ሜዳ ላይ እግር ኳስ አልነበረም” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ደቡብ ፖሊስ)

በጣም ይገርማል እናንተ ጋዜጠኛ ስለሆናችሁ ብቻ ነው የመጣሁት። በዚህ ሁኔታ ላይ አስተያየት መስጠት ይከብዳል። እግር ኳስ ስላልተጫወትን ምንም መግለጫ መስጠት አያስፈልግም። ዛሬ ሜዳ ላይ የታየው እግር ኳስ አልነበረም። ምክንያቱን ይሄ ነው አልልም። እናንተ አይታችዋል ። ጋዜጠኞች ስለሆናችሁ ራሳችሁ ብታወሩ ይሻላል፤ በናንተው ያምራል። በሶስተኛ እጅ ነው የተሸነፍነውው። ቡድኔ ግን የተሻለ ነው፤ በሚገባ ጥሩ ነበር። ስላከበርኳችሁ ብቻ ነው የመጣሁት። ስለ ቀጣይ ነገር ምንም ማለት አልፈልግም፤ አመሰግናለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡