እጅግ ደካማ እና አሰልቺ የነበረው የዛሬው የአዲስ አበባ ስታድየም የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
“ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች አሸንፈን የቡድናችንን የማሸነፍ መንፈስ ማምጣት ነው ትልቁ አላማችን” ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለጨዋታው
“ውጤቱ የሚገባን ነው ፤ ለማሸነፍ ካደረግነው ጥረት አንፃር። ጨዋታው አመርቂ አልነበረም ማሸነፋችን ግን የተሻለ ነገር እንድንሰራ እና ወደ ጥሩ መንፈስ እንድንገባ ያደርገናል ብዬ አስባለው።”
ስለቡድኑ የሜዳ ላይ ቅንጅት
“ገና ብዙ ይቀራል። ምክንያቱም የነበራቸውን በራስ መተማመን እና የጨዋታ ብቁነት ለማምጣት ብዙ ስራ ይጠይቃል። አሁንም እየሰራን ያለነው ይህንን ለማምጣት ነው። እናም ገና ነው ብዬ ነው እኔ የማስበው።”
ስለ ዋንጫ ፉክክሩ
“ስለዋንጫው አሁን መናገር አልፈልግም። እኛ ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች አሸንፈን የቡድናችንን የማሸነፍ መንፈስ ማምጣት ነው ትልቁ አላማችን።”
“ዳኞች ይችላሉ አይችሉም ? ይችላሉ ፤ ለምን ግን እንደሚሳሳቱ አላውቅም” ስምዖን አባይ – ድሬዳዋ ከተማ
“እንደእንቅስቃሴ በቡድኔ አልተከፋውም። የተሻለ የኳስ ፍሰት አሳይተናል። በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ባንጠቀምባቸውም ጥሩ የጎል ማግባት አጋጣሚዎች አግኝተናል። ካሉኝ ተጨዋቾች አንፃር አማካዮችን አብዝቼ ለመጫወት ሞክሪያለው። በኳስ ቁጥጥሩም ብልጫ መውሰድ ችለናል። ሆኖም ግን ብልጫ መውሰድ ብቻ ዋጋ የለውም ውጤቱን እነሱ ይዘውብን ሄደዋል። ግን እንደንቅስቃሴ የሚያስከፋ ነገር አላየሁም።”
ስለ ፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎቹ
“ስለ ፍፁም ቅጣት ምቱ ምንም መናገር አልፈልግም። የሚታይ ነገር ነው። ፍፁም ቅጣት ምት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ግን ጨዋታውን ያየው ሰው ይፍረድ።
ዳኞች ይችላሉ አይችሉም ? ይችላሉ ፤ ለምን ግን እንደሚሳሳቱ አላውቅም። በኔ ውሳኔውም አግባብነት ያለው አይመስለኝም ፤ ያየ ሰው ደግሞ ሊፈርድ ይችላል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡