ከ26ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማ ደደቢትን ያስተናገደበት ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ ወደ ድሬድዋ ተጉዞ 2-1 ከተሸነፈው ስብስብ ሮበርት ኦዶንካራ፣ ሱራፌል ዳንኤል፣ ኢስማኤል ሳንጋሬ እና ተስፋዬ በቀለን በማሳረፍ ጃኮ ፔንዜ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ፣ ሱሌይማን መሐመድ እና ፉአድ ፈረጅን ተክቶ ሲገባ በደደቢት በኩል ባህርዳርን 5-2 ካሸነፈው ስብስብ ኤፍሬም ጌታቸውን በአሸናፊ እንዳለ ተተክቶ ነበር ጨዋታውን የጀመረው።
ጨዋታው ገና እንደተጀመረ ነበር ጎል ያስተናገደው። 1ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን መሐመድ በግራ መስመር ይዞት በመግባት ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ማታውኪል ሲተፋው ሱሌይማን በድጋሚ አግኝቶ ለኤፍሬም ዘካርያስ አሻግሮለት ኤፍሬም በቀጥታ ወደግብ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ አዳማዎች መሪ መሆን ችለዋል። ገና ከጀረምሩ መነቃቃትን የፈጠሩት ባለጋሪዎቹ 7ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ኤፍሬም ዘካሪያስ ያሻማለትን ኳስ ቡልቻ ሹራ በአግባቡ ከተቆጣጠረ በኋለ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂ ባዳነበት ሙከራ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የቀረቡበት አጋጣሚ ነበር።
በመስመር በኩል ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች በቡልቻ ሹራ አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ታግዘው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማድረግ የደደቢት ተከላካዮችን ሲያስጨንቁ ውለዋል። 22ኛው ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ቡልቻ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ በቀጥታ ወደግብ አክርሮ ቢመታም ኢላማውን ያልጠበቀ ነበር። ደደቢቶች አራት ተከላካዮቻቸውን ከቦታቸው ሳይንቀሳቀሱ እንዲጫወቱ በማድረግ የአዳማን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት ቢሞክሩም ከርቀት የሚመቱ እና ተሻጋሪ ኳሶችን ኳሶችን መቆጣጠር ከብዷቸው ሲቸገሩ ተስተውሏል። በሙከራ ደረጃም ቢሆን 18ኛ ደቂቃ ላይ ኑሁ ፋሲይኒ ወደ ግብ አክርሮ የመታው እና ኢላማውን ያልጠበቀው ብቸኛ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር።
35ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመርያ ተሰላፊነት እድል ያገኘው ወጣቱ አማካይ ፉአድ ፈረጃ ከርቀት ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ሲወጣበት ከአንድ ደቂቃ በኋላ በድጋሚ ከሳጥን ውጭ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል። 43ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቡልቻ ከቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ አሻግሮለት ዱላ ሙላቱ ወደግብ ለመምታት ሲሞክር ኳሱን ሳያገኘው ሚዛኑን ስቶት ቢወድቅም በድጋሚ ተነስቶ ሲሞክር ተጨራርፎ ፉአድ ፈረጃ ጋር ደርሶ ወጣቱ አማካይ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። እነዚህ ጎሎችም ለፉአድ በአዳማ ማልያ የመጀመርያ ጎሎች ሆነው ተመዝግበውለታል።
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ቡልቻ ሹራ ሁለት ተጫዋቾች አልፎ ወደ ግብ የሞክራትን ግብ ጠባቂው ሲያድንበት ከ10 ደቂቃዎች በኋላ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቡልቻ ከግራ መስመር ሱሌይማን መሐመድ ከሳጥን ውጭ ያሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ወደ ግብነት በመቀየር ልዩነቱን ወደ 4 አድርሷል።
አዳማዎች ከግቡ መቆጠር በኋላም በተደጋጋሚ ሙከራ መድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማግኝት አልቻሉም። ደደቢቶች በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ወደ ግብ የደረሱት ሲሆን 58ኛው ደቂቃ ላይ መድሃኔ ታደሰ የግብ ጠባቂ ስህተት ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ በቴዎድሮስ በቀለ የተጨናገፈበት፤ 59ኛው ደቂቃ ላይ በተከላካዮች ተገጭቶ የተመለስ ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አንቶኒሆ አባዋላ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበት እንዲሁም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ኑሁ ፋሴይኒ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ናቸው።
ውጤቱን ተከትሎ የደደቢት እግርኳስ ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2002 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ መውረዱን ሲያረጋግጥ አዳማ ከተማ በአንፃሩ በ33 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡