26ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አዳማ ከተማ ደደቢትን አስተናግዶ 4-0 ማሸነፍ ችሏል። ከጨዋታው በኋላም አሰልጣኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
”ከሌላው ጊዜ በተሻለ ያገኘነውን አጋጣሚ በመጠቀማችን ይሄን ውጤት ይዘን ልንወጣ ችለናል” አስቻለው ኃይለሚካኤል (አዳማ ከተማ)
ስለ ጨዋታው
በዚህ አጋጣሚ ለአዳማ ደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። የዛሬ ጨዋታ እንዳያችሁት ከሌላው ጊዜ የተሻላ ያገኘነውን አጋጣሚ በመጠቀማችን ይሄን ውጤት ይዘን ልንወጣ ችለናል። ከዚህ ቀደምም ስህተቶቻችንን አይተን ነው ልምምዶች የምንሰራው። ከደካማ ጎኖቻችን በመነሳት ነው ለጨዋታ የምንዘጋጀው። የአጨራረስ እና አዕምሮ ዝግጅት ላይም አተኩረን በመስራት ነበር የቀረብነው። እንደዚህም ሆኖ ብዙ ኳስ ስተናል። መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች እናስተካክላለን።
ዛሬ ከሌሎች ጨዋታዎች የተለዩ ነገሮች
ደጋፊዎች ዛሬ ከመጀመሪያው ጀምሮ አበረታተዋል። እና ይሄ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሮልናል። ያ ነገር ለተጫዋቾች ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል። ተጫዋቾቹም በግልም ከኛ ጋርም ተነጋግረናል።
”የእኛ ተጫዋቾች ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ መፍዘዝ ይታይባቸው ነበር ” ዳንኤል ፀሐዬ (ደደቢት)
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው እንዳያችሁት የእኛ ተጫዋቾች ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ መፍዘዝ ይታይባቸው ነበር። ያንን ተጠቅመውም ገና እንደ ተጀመረ ነበር ግብ የተቆጠረብን። የተወሰኑ ደቂቃዎችን ግብ እንዳይቆጠርብን ማድረግ ችለን ነበር። ከዛ በኋላ ግን ሁለት ሶስት ግቦች ተቆጠሩብን። ተጫዋቾችም ሆነ ቡድኑ ወደሚፈለገው ደረጃ አልመጣንም። አዳማ ከኛ የተሻለ ነበር፤ ከዛ በላይ ግን እኛ ጥሩ አልነበርንም ።
ስለ ደደቢት መውረዱን ማረጋገጥ እና ቀጣይ እጣ ፈንታ
በርግጥ ይሄ ጥያቄ ለእኔ ሳይሆን ለማኔጅመንቱ ነው መጠየቅ ያለበት። ቢሆንም ግን እንደ ቡድን ድጋሚ ወደ ላይ ይዤ ለመውጣት ጥረት አደርጋለሁ። ዘንድሮ በበጀት እጥረት ብዙ ችግሮች አጋጥሞን ነበር።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡