ሀ-20 ምድብ ሀ | ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ድል አስመዝግበዋል

14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና አሸንፏል። ሀዋሳ እና መከላከያ ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ ሲጥሉ ቅዱስ ጊዮርጊስም የፎርፌ አሸናፊ ሆኗል።

ረፋድ 4:00 ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፋል። በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች በአብዱልፈታህ ዓሊ የሚመራው የመሐል ክፍላቸው ብልጫ ወስደው ኳሶችን ማንሸራሸር ቢችሉም የወላይታ ድቻ የተከላካይ መስመር ግን በቀላሉ የሚቀመስ አልነበረም። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ባለሜዳዎቹ ብልጫን ወስደው በመጫወት ጥቃት መፈፀም ችለዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ታምራት ስላስ ከቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሲያሻግር መልካሙ ቦኬ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት አስቆጪ ሙከራ ነበረች። በዚህች ሙከራ የተነቃቁት ድቻዎች 14ኛው ደቂቃ ንጉሴ ተከስተ ያሻማውን ኳስ የድሬዳዋን የተከላካይ መስመር ኳስ ሊቆጣጠሩ ባለመቻላቸው ታምራት ስላስ ተንሸራቶ በመውረድ ግብ በማድረግ መሪ መሆን ችለዋል። ከዚህ ውጭ ዲቻዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴን ሲደርግ በነበረው ንጉሴ ተከስተ ሙከራ ቢያደርጉም የድሬዳዋው ግብ ጠባቂ አብዩ ካሳየ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ እንደምንም አውጥቶበታል። በድሬዳዋ በኩል በብቸኝነት የምትጠቀሰው ሙከራ ያሬድ አመርጋ በራሱ ጥረት ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ለዳዊት አበበ ሰጥቶት ሞክሮ በአግዳሚው የወጣችበት ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የኳስ ቁጥጥር በሁለቱም በኩል የተመለከትን ሲሆን ብልጫ የነበራቸው ድቻዎች ሁለት ለግብ የተቃረበ ሙከራ አድርገዋል። በድሬዳዋ ተከላካዮች ስትመለስት ያገኛትን ኳስ ታምራት ስላስ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ ለጥቂት የወጣችበት እና ንፍታለም ታፈሰ በአግዳሚው የወጣችበት ኳስ ነበሩ። ግብ ለማግባት ከመፈለጋቸው የተነሳ ተከላካዮቻቸውን ወደ ፊት አስጠግተው ሲጫወቱ የነበሩት ድሬዳዋዎች ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ነበሩ። 85ኛው ደቂቃ ላይም በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ታምራት ስላስ ተከላካዩ አስግዶም ዝናቡን በማለፍ በድንቅ አጨራራስ ወደ ግብነት በመቀየር ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ልዩነቱን ከፍ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው መገባደጃ ተስፋሁን ሙሉጌታ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የላካትን ኳስ ተቀይሮ በመግባት ድንቅ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ንፍታልም ታፈሰ በግሩም የጭንቅላት ኳስ የቡድኑ መደምደሚያ ግብ አስቆጥሮ በወላይታ ድቻ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። (በሚሊዮን ኃይሌ)

08:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታድየም ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ኳሱን ተቆጣጥረው ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ በተለይ በየነ ባንጃ ከግራ መስመር ወደ ቀኝ ሰብሮ በመግባት ለአጥቂዎቹ የሚፈጥረው የግብ ዕድሎች ለሲዳማ ቡና ተከላካዮች ፈተና ነበር። አምበሉ ፉአድ ነስሮ ወደ ፊት ኳሱን ይዞ በመግባት በቀጥታ ለኪቲማ ጅማ ያቀበለውን ኪቲማ ኳስ ወደ ጎሉ አጠንክሮ በመምታት ለጥቂት ወደ ውጭ የወበት በቡናዎች በኩል የመጀመርያው የግብ ሙከራ ነበር። የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ሲዳማዎች አብዝተው በራሳቸው ሜዳ መከላከልን ምርጫቸው በማድረጋቸው ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ክፍል በመግባት የፈጠሩት ምንም አይነት የግብ እድል አልነበረም።

በ2008 የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አምበል ሆኖ የምናውቀውና የመከላከያ ተስፋ ቡድን የተጫወተው አሁን በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው አማካዩ ማቲዮስ ወ/አረጋይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው ሲሆን ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ አናት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። አልፎ አልፎም ቢሆን ወደ ፊት በመሄድ መጫወት የቻሉት ሲዳማዎች በፍቅር ግዛቸው አማካኝነት የፈጠሩት የግብ ዕድል በኢትዮጵያ ቡና ግብጠባቂ ዳዊት ባህሩ ከሽፏል። 31ኛው ደቂቃ በሲዳማ ቡና የግብ ክልል ከተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ነፃ ኳስ ያገኘው ኤፍሬም ታደሰ ወደ ጎልነት በመቀየር ኢትዮጵያ ቡናዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል ዕድል በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሙሴ ከበላ ከመሐል ወደ ቀኝ መስመር የጣለለትን ኪቲማ ወደ ጎል ቢመታውም የሲዳማ ቡና ግብጠባቂ ዳግም ለገሠ አድኖበታል።

ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሳይሆን ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ብንመለከትም በአንፃራዊነት ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። ሆኖም የጎል እድል የሚፈጥሩበት መንገድ በክፍት ሜዳ ሳይሆን ከቆሙ ኳሶች በመሆኑ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሲዳማዎች ከሳጥን ውጭ ያገኙትን ቅጣት በፍቅሩ ግዛቸው በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን የቡናዎቹ ግብጠባቂው ዳዊት ባህሩ አድኖበታል። ብዙም ሳይቆኝ ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ቦንኬ ቱንሲሣ የመታውን በድጋሚ የቡናዎቹ ዳዊት ባህሩ በጥሩ ሁኔታ መልሶበታል። መነሻውን በኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ያደረገው የቡናዎቹ ግብ ጠባቂ ዳዊት ባህሩ ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልበት ግብጠባቂ መሆኑን ዛሬም አስመስክሯል። በመጨረሻም ብልጫ የተወሰደባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የሲዳማዎችን ስህተት ተከትሎ የተገኘውን የግብ ዕድል ተቀይሮ በገባው ገዛኸኝ ደሳለኝ በመጠቀም ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። (በዳንኤል መስፍን)

በሌሎች የዚህ ምድብ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከውድድሩ ራሱን ያገለለው ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን በፎርፌ በማሸነፍ የምድቡ መሪ መሆን ሲችል ወደ አምቦ ያመራው ሀዋሳ ከተማ ከአምቦ ጎል ፕሮጀክት፤ ወደ አሰላ ያመራው መከላከያ ደግሞ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡