ሀ-20 ምድብ ለ | አዳማ ከተማ በመሪነቱ ሲቀጥል ተከታዮቹም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ 14ኛ ሳምንት ትላንት ተጀምሮ ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጠናቀቅ በሜዳው ሀላባን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 3-0 አሸንፎ ወደ መሪነት ተመልሷል። አአ ከተማ፣ ፋሲል እና መድንም ድል ቀንቷቸዋል።

4:00 ሰዓት ሊደረግ የነበረው ይህ ጨዋታ አዳማ ከተማ ላይ የመንግስት ከፍተኛ ባለ ስልጣናት ስብሰባ በመኖሩ ምክንያት ወደ 7:00 ሰዓት ተቀይሮ ተከናውኗል። በመጀመሪያው አጋማሽ ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃውች ላይ ተጭነው በመጫወት አዳማዎች ግብ ለማግኝት አልተቸገሩም። 9ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዘር ሲሳይ ከሳጥን ውጭ ወደግብ አክርሮ ከግቡ አግዳሚ ጋር በማጋጨት አስቆጥሮ አዳማን ቀዳሚ አድርጓል። አዳማዎች ከጎሉ በተጨማሪ በርካታ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ሲሆን 42ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዘር አሰፈ በመስመር ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ለዮናስ አብነት አሻግሮለት ዮናስ ወደግብ አክርሮ የመታው የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር። በሀላባ ከነማ በኩል የተሻለ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቡድኑ አምበል ፍቅረየሱስ ፀሀይ 27ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረ ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበት በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር የቻሉት ሁለቱም ቡድኖች ቢሆኑም ስኬታማ የነበሩት ግን አዳማ ከነማዎች ነበሩ። 71ኛው ደቂቃ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮ ቀጥታ ወደግብ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ሲያሰፉ 78ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የአብስራ አክሊሉ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተጠቅሞ በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ተጠግቶ የወጣው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ በድጋሚ የአብስራ አክሊሉ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያገኝውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ የግብ ልዩነቱን ወደ ሶስት ከፍ በማድረግ ጨዋታው በአዳማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድቡ ሌሎች ጨዋታዎች ትላንት የተደረጉ ሲሆን ከሜዳቸው የተጫወቱት ኢትዮጵያ መድን ወልቂጤ ከተማን፤ ፋሲል ከነማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በተመሳሳይ 1-0 አሸንፈዋል። አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ አፍሮ ፅዮንን 2-0 ረቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡