የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ሲከናወኑ መሪው ሰበታ ከተማ ከተማ እና ተከታዩ ለገጣፎ አሸንፈዋል። ደሴ ከተማም ወደ ሦስተኛ ከፍ ብሏል።
ወደ ቡራዩ ያቀናው የምድቡ መሪ ሰበታ ከተማ 1-0 አሸንፎ በመመለስ የአራት ነጥብ ልዩነቱን አስጠብቋል። በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ የሚገኘውና ለቡድኑ ውጤታማነት ወሳኘሰ ጎሎችን እያስቆጠረ የሚገኘው ናትናኤል ጋንቹላ በ21ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ለሰበታ ወሳኝ ሦስት ነጥብን አስገኝቷል። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጨዋታው ብርቱ ፉክክር ታይቶበታል። ተጋጣሚያችን ጠንካራ የነበረ ቢሆንም አሸንፈን ወጥተናል። አሁን ላይ ቡድናችን ላይ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚደርገው ጉዞ በእጁ ላይ ነው ያለው። በሜዳችን ያሉትን ሁለት ጨዋታዎች የማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ እናድጋለን።” ሲሉ አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ሰበታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ ከ2003 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ይሆናል።
ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ ፌዴራል ፖሊስን 2-0 በማሸነፍ የማደግ ጭላንጭል ተስፋውን አስቀጥሏል። በ40ኛው ደቂቃ ዳዊት ቀለመወርቅ ቀዳሚ የምታደርገዋን ግብ አስቆጥሮ ወደ እረፍት ሲያመሩ በ80ኛው ደቂቃ ብሩክ መርጊያ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ለገጣፎ 2-0 አሸንፏል።
ደሴ ላይ ደሴ ከተማን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ በደሴ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። አላዛር ዝናቡ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ባገባው ጎል ባለሜዳዎቹ ቀዳሚ ቢሆኑም ብዙም ሳይቆይ ታፈሰ ተስፋዬ ኤሌክትሪክን በ28ኛው ደቂቃ አቻ ማድረግ ችሎ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ተጨማሪ ደቂቃዎች ሲቀሩ በድሩ ኑር ሑሴን በፍፁም ቅጣት ምት ደሴ ከተማን አሸናፊ ማድረግ የቻለበትን ድል አስቆጥሯል። ውጤቱ ኤሌክትሪክን ከፉክክሩ ሲያስወጣው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለውና በሁለተኛው ዙር እጅግ ከፍተኛ መሻሻልን ያሳየው ደሴ ከተማ በሒሳብ ስሌት የማደግ ጭላንጭል ተስፋ መያዝ ችሏል።
ወሎ ላይ ወሎ ኮምበልቻ አውስኮድን በነቢዩ አህመድ የ57ኛ ደቂቃ ጎል 1-0 ሲያሸንፍ ወልዲያ በሜዳው አክሱም ከተማን በ59ኛው ደቂቃ ላይ እንድሪስ ሰይድ በፍፁም ቅጣት ምት፣ በ90ኛው ደቂቃ ተስፋዬ ነጋሽ በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 አሸንፏል። ዱከም ላይ ገላን ከ አቃቂ ቃሊቲ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡