የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ሲከናወኑ ሀዲያ ሆሳዕና ለፕሪምየር ሊጉ በእጅጉ የተቃረበበትን ድል ከሜዳው ውጪ አስመዝግቧል። ተከታዮቹ አርባምንጭ እና ስልጤ ወራቤም አሽነፈዋል።
ወደ ቢሾፍቱ ያመራው ሀዲያ ሆሳዕና ቅዳሜ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ገጥሞ 2-0 በማሸነፍ የ6 ነጥብ ልዩነቱን አስጠብቋል። በመከላካያ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተከናወነው ይህ ጨዋታ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጀምሮ ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በ13ኛው ደቂቃ ላይ ጫለ ከበደ ከርቀት ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት ኳስም በባለ ሜዳዎቹ በኩል የመጀመሪያ ሙከራ ሆኗል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩልም ኤሪክ ሙራንዳ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከርቀት የሞከረው ኳስ ለጥቂት ነበር ወደ ላይ የወጣችበት። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ሆሳዕናዎች የሜዳውን የመሐል ክፍል እንቅስቃሴ ብልጫ በመውሰድ ላይ አመዝነው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም እንቅስቃሴ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዮሴፍ ድንገቱ በ17ኛው ደቂቃ ላይ ለእዩኤል ሳሙኤል የሰነጠቀለት ኳስ እዩኤል በአግባቡ በመቆጣጠር ሁለት ተጫዎቾችን በማሸማቀቅ በግራ እግሩ አክርሮ መትቶ ከመረብ በማሳረፍ ሆሳዕናን ቀዳሚ አድርጓል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ቢሾፍቱዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ሲጫወቱ በርካታ የጎል አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችለዋል። በ27ኛው ደቂቃ ሚካኤል ታመነ በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ አክርሮ መትቶ የግቡን አግዳሚ ተጠግቶ የወጣበት፤ በ33ኛው ደቂቃ ሚካኤል ታመነ በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ ለወጠው ሲባል ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም በ39ኛው ደቂቃ ላይ ጫላ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሲሳይ አማረ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሲመልሰው ሚሊዮን ብሬ አግኝቶ በድጋሚ ቢመታውም የሆሳዕና ተከላካይ አዩብ በቀታ ኳሷን መረብ ላይ እንዳታርፍ ያደረጋት ሙከራዎች በቢሾፍቱ በኩል ተጠቃሽ ነበሩ። የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በግማሽ ዓመቱ ሆሳዕናን የተቀላቀለው ሱራፌል ጌታቸው ለኤሪክ ሙራንዳ ያሻገረውን ኳስ ኬኒያዊው አጥቂ ገፍቶ በመግባት የግብ ጠባቂውን አቋቋም ባሳተ መልኩ ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎ ነብሮቹ 2-0 እንዲመሩ አስችሏል።
በሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ባለሜዳዎቹ በእንቅስቃሴ እንዲሁም ወደ ግብ በመቅረብ እጅጉን ተሽለው ታይተዋል። በተቃራኒው ሆሳዕናዎች ባልተመጠኑ ቅብብሎች እና በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በሆነ እንቅስቃሴያቸው ሳቢያ ጥረታቸው አውቶሞቲቭን መፈተን ሳይችል ቀርቷል። ባለሜዳዎቹ ከመስመር ላይ በሚሻገሩ ኳሶች ማጥቃታቸውን በመቀጠል 48ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ታሪኩ እሸቴ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ላይ ሲወጣ ከአራት ደቂቃ በኋላ ሲሳይ አማረ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። 79ኛው ደቂቃ ላይ አዩብ በቀታ በሰራው ስህተት ሚካኤል አግኝቶ ወደ ግብነት ለውጠው ሲባል በጨዋታው ጥሩ አቋም ያሳየው ግብ ጣባቂ ኳሱን አድኖበታል። የጨዋታው ደቂቃ ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ ቀዝቃዛ እንቅስቅሴ የታየ ሲሆን በሆሳዕና በኩል እዩኤል ከርቀት የመታው እንዲሁም ከማዕዘን የታሻገረውን ኳስ አዮብ በቃታ በግንባሩ ሞክሮ ሳይሳካ የቀረበት በሆሳዕና በኩል የሚጠቁ ናቸው። በጨዋታው በ69ኛው ደቂቃ ላይ ውሻ ሜዳ ውስጥ በመግባት የተመልካችን ቀልብ የሳበ ክስተት ተፈጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎ ሦስት ጨዋታዎች ብቻ በሚቀሩት የምድብ ሐ በ7 ነጥቦች ከተከታዩ የራቀው ሀዲያ ሆሳዕና ቀጣዩን ጨዋታ ካሸነፈ በቀጥታ ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባቱን ያረጋግጣል።
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ነገሌ ቦረናን አስተናግዶ 4-0 አሸንፏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ግብ ተጠናቆ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ
ስንታየሁ መንግስቱ በ47ኛው እና በ67ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር እሱባለው ፍቅሬ በ76ኛው ደቂቃ እንዲሁም አሸናፊ ተገኝ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች 4-0 አሸንፏል።
ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ከ ቡታጅራ ያደረጉት ጨዋታ በስልጤ ወራቤ 2-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሺንሺቾ ላይ ከምባታ ሺንሺቾ በብርሀኑ ኦርዴሎ ሁለት ጎሎች ነቀምት ከተማን 2-1 አሸንፏል። ለነቀምት ከተማ እስራኤል ታደሰ ብቸኛውን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው። ጅማ ላይ ጅማ አባ ቡና ከሻሸመኔ ያደረጉት በጅማ አባ ቡና 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ካሚል ረሺድ በ11ኛው ደቂቃ ብቸኛውን የማሸነፍያ ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ሚዛን አማን ላይ ቤንች ማጂ ቡና ከ ካፋ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የክለቡ ደጋፊ ለነበሩት ህይወታቸው ላለፈው አቶ አህመድ ጠይብ የ1 ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ነበር የተጀመረው። በጨዋታው ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት የሚመስል አጨዋወት ሲተገብሩ የነበሩት ካፋ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎም ወደ ፊት ለአጥቂው ኦኒ ኡጁሉ ለማድረስ ቢሞክሩም ኳሱ በመቋረጥ የተፈለገው ስፍራ ሊደርስ አልቻለም። ባለሜዳዎቹ በፊት መስመር አጥቂዎቹ ወንድማገኝ ኬራ እና ኤሪክ ኮልማን በተደጋጋሚ ወደ ግብ ቢደርሱም ኳስን ከመረብ ማገናኘት አልቻሉም። በተለይ ወንድማገኝ የካፋ ቡና ግብ ጠባቂ መውጣትን ተመልክቶ ከፍ አድርጎ የላካት ኳስ የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣችበት እንዲሁም ጋናዊዉ አጥቂ ኤሪክ ኮልማን ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታትና የወጣችበት ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ ባሜዳዎቹ የአሰላለፍ ቅርፁን በመቀየር እንዲሁም አጥቂው ወንድማገኝን በፎሳ ሴንዴቦ በመቀየር የአጥቂ ቁጥሩን ከፍ አድርጎ ድል ማስመዝገብ ችሏል። በ58ኛው ደቂቃ ካፋ ቡናዎች አምበላቸው ምንተስኖት በመስመር በኩል አልፎ ወደ ግብ የላካት ኳስ በግብ ጠባቂዉ ጥረት ግብ ከመሆን የዳነችው አስቆጪ አጋጣሚ ስትሆን በ83ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር ያገኘውን ኳስ ተቀይሮ የገባዉ ፎሳ ሴንዴቦ ወደ ግብ ቀይሮ ጨዋታው በቤንች ማጂ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡