በፈረንሳይ አስተናጋጅነት ለስምንተኛ ጊዜ የሚከናወነው የፊፋ የዓለም ሴቶች ዋንጫ ከጁን 7 – ጁላይ 7 ድረስ በ24 ሀገሮች መካከል ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ላይ ለመዳኘት ከተመረጡት ዳኞች አንዷ የሆነችው ሊዲያ ታፈሰም ነገ ወደ ፈረንሳይ ታቀናለች።
በተለያዩ ጊዜያት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በብቃት እየመራች የምትገኘው ሊዲያ ታፈሰ ወደ ፈረንሳይ ከማቅናቷ አስቀድሞ በጉዟዎ ስለምታልምው ነገር ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋ ይሄን ብላለች።
” እንደማንኛውም ዳኛ ብዙ ነገር አስባለው። ከመክፈቻው ጨዋታ የምድብ ጨዋታ ፣ የሩብ ፍፃሜ ፣ የግማሽ ፍፃሜ እያልኩ እስከ ፍፃሜው ጨዋታ ድረስ ያሉትን ጨዋታዎች መዳኘትን አስባለው። መዘጋጀት የሚገቡኝን ነገሮች ሁሉ በሚገባ ተዘጋጅቻለው። በሀገር ውስጥ ከወንዶች ፕሪምየር ሊግ እስከ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በመዳኘት፣ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ወቅታዊ አቋሜን ለመፈተሽ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅቻለው። እዛም ከሄድኩ በኃላ የሚሰጡትን ስልጠናዎች በመቀበል ስራዬን ለመስራት አስባለው። እንግዲህ ስራዬ እንዲሳካ ለሁሉም ነገር ፈጣሪ ይጨመርበት። የተሻሉ ውድድሮችን በመምራት የሚሰጡኝንም ጨዋታዎች ላይ በጥሩ ብቃት በማሳየት ውድድሩን አጠናቅቄ መምጣት አስባለው።”
ሊዲያ በ2015 በካናዳ የዓለም ሴቶች ዋንጫ፣ በ2016 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ እና የጆርዳን ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ፣ በ2018 የፈረንሳይ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ፣ የጋና አፍሪካ ዋንጫ ጨምሮ በርካታ የማጣርያ ውድድሮችን መምራት የቻለች ስኬታማ ዳኛ ናት።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡