ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ዙሪያ ቅሬታውን አሰምቷል

ከአሰላ ወደ ቢሾፍቱ ተለውጦ 0-0 በተጠናቀቀው የሀዋሳ እና ቡና ጨዋታ ዙሪያ ሀዋሳ ከተማ በተጫዋቾቼ እና በመኪናችን ላይ ጥቃት ተፈፅሟል በማለት ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ አሰምቷል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ በሜዳው እንዳይጫወት በመቀጣቱ ምክንያት አሰላ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን መግጠሙ ይታወሳል። ሆኖም ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ በጣለው ዝናብ ምክንያት ሜዳው አላጫውት በማለቱ የዕለቱ ዳኞች ጨዋታውን ወደ አዳማ ለውጠውት የነበረ ሲሆን ምሽት ላይ በድጋሚ ቢሾፍቱ ላይ እንዲከናወን ተወስኖ ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በቢሾፍቱ ተደርጎ 0-0 ተጠናቋል።

ሆኖም ሀዋሳ ከተማ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ ባስ ሲገቡ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በነሱም በባሱም ላይ ጥቃት መሰንዘሩን በመግለፅ ጉዳዩን ለዕለቱ ኮሚሽነር እና ለፌድሬሽኑ ማሳወቁን በቡድን መሪው አቶ ዱሬሳ ዱካሞ በኩል በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። አቶ ዱሬሳ ጨምረውም በሰዓቱ የክለቡ ተጫዋቾች ያኦ ኦሊቨር ፣ እስራኤል እሸቱ እና ወንድምአገኝ ማዕረግ ላይ መጠነኛ ጉዳት በመድረሱ ወደ ህክምና ለመሄድ እንደተገደዱ ገልፀው ጉዳዩን በቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመገኘት እንዳስመዘገቡም አስረድተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡