” የአሰልጣኝነት ጅማሬዬ ጥሩ ነው፤ በዚሁ እቀጥላለሁ” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

እግር ኳስን በሀዋሳ ቢ ቡድን ውስጥ ነበር ጅማሮን ያደረገው። በዋና ቡድን ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወተው ወላይታ ፔፕሲ ለተባለ ክለብ ሲሆን በመቀጠል ዲላ ከተማ፣ ፊንጫ ስኳር፣ ሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ እና ለረጅም ዓመታት በአምበልነት ጭምር በሲዳማ ቡና መጫወት ችሏል፡፡ በ2007 ከእግር ኳሱ ከተገለለ በኋላ በወሰደው የC ላይሰንስ የአሰልጣኝነት ኮርስ ታግዞ 2008 ላይ ከ17 ዓመት በታች የሲዳማ ቡናን ቡድን በመያዝ የአሰልጣኝነት ሙያን ሀ ብሎ ጀምሯል፡፡ በፈጣን ሁኔታ ራሱን በማጎልበትም የሲዳማ ቡና ዋናው ክለብ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን እስከ 2010 ግማሽ ዓመት ሰርቷል። በመቀጠል ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ ጊዜያዊ አሰልጣኝ በመሆን ቡድኑን ተረክቦ ከወራጅ ቀጠናው በማራቅ 2010ን አጠናቋል፡፡ ዘንድሮ በሁለት አመት የውል ኮንትራት ተሰጥቶት የሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ በመሆን እየሰራ ያለው ወጣቱ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ዘንድሮ እያሳየ ስላለው የቡድኑ የዋንጫ ተፎካካሪነት ብሎም ስለ አጠቃላይ የእግር ኳስ ህይወቱ እና የአሰልጣኝነት ሙያው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
እግር ኳስ መጫወት አቁመህ ወደ አሰልጣኝነት የገባኸው በቅርብ ነው። ስለ አሰልጣኝነት አጀማመርህ ብናወራ?

አሰልጣኝነትን 2008 የሲዳማ ቡና ከ17 ዓመት በታች ቡድንን በመያዝ ነበር የጀመርኩት። በቆይታዬ ቡድኑ ሁለተኛ በመውጣት ነበር ያጠናቀቀው፡፡ 2009 ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ወደ ዋናው ቡድን ሄድኩ፡፡ 2010 ላይ ደግሞ በሁለተኛው ዙር የዓለማየሁ ዓባይነህን መልቀቅ ተከትሎ በጊዜያዊነት ዋና አሰልጣኝ በመሆን ዙሩን ማጠናቀቅ ቻልኩ፡፡ በወቅቱ ጥሩ ውጤት ነበር ያስመዘገብነው። ማለትም በመጀመሪያው ዙር 18 ነጥቦችን ሰብስበን ነው ማጠናቀቅ የቻልነው፡፡ በሁለተኛው ዙር ግን 25 ነጥቦችን ሰብስበን ነው ቡድናችንን ከመውረድ ያተረፍነው፡፡ ጥሩ ውጤት በማምጣቴ ክለቡ በቋሚነት እንዳሰለጥን ጥያቄ ሲያቀርቡልኝ እሱን በመቀበል ተስማምቼ እያሰለጠንኩ፤ በጥሩ ሁኔታም አንደኛውን ዓመት እያገባደድን እዚህ ደርሰናል።

አሰልጣኝነት እጅግ ከባድ ነው ብዙ ጫናዎች አሉት። ያንን ነገር ደግሞ መቋቋም መቻል አለብህ፡፡ ምክንያቱም ቡድናችን ለዋንጫ እየተፎካከረ ነው። ውጤት ከመፈለግ አንፃር ጫና ይኖራል። ያንን ነገር መረዳት ካልቻልክ እና ጠንክረህ ካልሰራህ እጅግ ከባድ ሙያ ነው። ጠንካራ መሆን ይጠበቅብሀል። በስራው ትዕግስተኛም መሆን አለብህ። አሁን ባለው መንገድ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዋች ነጥብ እያመጣን ነጥባችን ያደረሰን ደረጃ ይዘን ማጠናቀቅ ነው ሀሳባችን፡፡

ወደ ክለብ አሰልጣኝነት ስትመጣ እንዴት ልምድ የሌለው አሰልጣኝ ይመጣል የሚሉ አይጠፉም። ያንን ጊዜ አልፈህ መጥተህ ቡድህ ተፎካካሪ ሲሆን ከተነሱት ነገሮች አንፃር ምን ተሰማህ?

ልምድ አለው የለውም የሚባሉ ነገሮች እኔ ጋር አልመጡም። በውጭ ሊወራ ይችላል፤ ክለቡ ግን ያለ ጥርጥር አምና በሁለተኛው ዙር እንድረከብ ሲያደርጉኝ በሙሉ መተማመን ነበር። ምክንያቱም በቡድኑ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ቆይቻለው፤ ተጫዋቾቹንም ስለማውቃቸው ወደ አንድነት በማምጣት ነው የዛን ዓመት ውድድራችንን የጨረስነው። ከአንደኛው ዙር የተሻለ ውጤት ስላስመዘገብኩ ቋሚ ስራውን ለኔ እንደሚሰጡኝ በጣም እርግጠኛ ነበርኩ። ሲዳማ ቡና ትልቅ ክለብ ስለሆነ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ያስፈልገዋል ተብሎ ሊወራ ይችላል፤ ለምን ተወራ ማለትም አትችልም። ክለቡ ግን ከኔ ጋር የተነጋገረው በክፍያ ዙሪያ ነው እንጂ ስለልምድ አልነበረም። ከጅምሩ በራሴ እምነት ነበረኝ። ምናልባት ከውጤት መፈለግ አንፃር ምናልባት ሊሉ የሚችሉ ይኖራሉ። እኔ የምፈልጋቸውን ተጫዋቾች አስፈርሙ፤ ዋንጫ እናነሳለን ነበር ያልኳቸው። ሰባት ተጫዋቾች ሰጥቼ ነበር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከምፈልጋቸው ተጫዋቾች ማንንም አላስፈረምኩም። የፈለኳቸውን ማግኘት ባንችል እንኳን ተፎካካሪ ለመሆን ከዚህ በፊት የነበሩንን ሪከርዶች አሻሽለን በጥሩ ደረጃ እንጨርሳለን በሚል ነበር ከቦርድ ጋር ቃል በቃል ያወራነው።

ልምድ የሌለው በመሆኔ ለኔ የከበደኝ ነገር የለም። አንደኛ ቡድን ላይ ስትሰራ ምን መስራት አለብህ የሚለው ወሳኝ ነው። በክለቡ ረጅም ዓመት በተጫዋችነት ስለቆየሁና ለአሰልጣኞች ቅርብ ስለሆንኩ አላስቸገረኝም። ሌላው ወሳኝ ጉዳይ የተጫዋቾች ማኔጅመንት ነው፤ ልምምድ ላይ በምታሰራው ብቻ አይደለም ውጤታማ የምትሆነው። ለምሳሌ ሲዳማ ቡና ውስጥ ከያዝኳቸው ተጫዋቾች ውስጥ አንድም በዚህ ዓመት ሜዳ ገብቶ ያልተጫወተ የለም። እንደየጨዋታው እና ሜዳው ባህርይ ተጫዋቾች እና አጨዋወት እየቀየርን ነው የምንጫወተው።

ደጋፊዎች አሁን ብትጠይቃቸው በኔ ደስተኛ ናቸው። ብዙ ጊዜ ወጣት አሰልጣኞች ሲቸገሩ ሰለሚስተዋል ነው ስጋት የሚመጣው። የሚሰጉት ደግሞ ክለባቸውን ስለሚወዱ እንጂ እኔ ቡድኑን እንዳልይዘው ወይም ጥላቻ አይደለም። ውጤቱ ምንም ይሁን ኃላፊነቱን ለሱ ስጡት የሚሉ ደጋፊዎችም ነበሩ። ክለባችን በወጣቶች የተገነባ ነው። ትንሽ ወጪ አውጥተን ከከፍተኛ ሊግ ባመጣናቸው ተጫዋቾች እና አምስት ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ነው እየተጠቀምን ያለነው። አንደኛ ወጪ ቆጥበን፣ ሁለተኛ ለሀገራችን ለወደፊቱ ተስፋ ያለቸውን ወጣቶች አፍርተናል። በዚህ ደፍረህ መስራት በራሱ በራስ መተማመንን ይጠይቃል። እኔ ወደ አሰልጣኝነት ስመጣም በወጣቶች ትኩረት አድርጌ መስራት እንዳለብኝ ለሀገርም የሆነ ነገር መቀየር አለብኝ ብዬ ነበር ያሰብኩት። ጅማሬዬ ጥሩ ነው፤ በዚው እቀጥላለው።

ቡድንህ በአብዛኛው ስብስቡ ከከፍተኛ ሊግ ነው። አጀማመራችሁ የዋንጫ ተፎካካሪ አይመስልም ነበር። አሁን ግን ወደ ተፎካካሪነት መጥቷል። ይህ ሒደት ላንት ምን ትምህርት ሰጥቶሀል?

ምን መሰለህ ክለባችን ወጣ ገባ ሊመስል ይችላል፤ ግን በኔ አይደለም። ምክንያቱም ከሜዳችን ውጭ የምናገኛቸው ክለቦች በጣም ጠንካራ እና ብዙ ደጋፊ ያላቸው ቡድኖችን ነው። በተጨማሪም በዳኝነት እና በተለያየ ነገር ነርም ቢሆን ያው በጠባብ ውጤት ነው የምንሸነፈው። ከሜዳ ስንወጣ የምናገኛቸው ቡድኖች ወደ ዋንጫ የቀረቡ ቡድኖች ናቸው። ልምድ ያላቸው ጠንካራ ቡድኖች ስለነበሩ ቡድናችን ጥሩ እየተጫወተ በእቅስቃሴ በልጦ በጥቃቅን ስህተቶች ነው ተሸንፈን የምንወጣው። በሜዳችን ስንጫወት ግን ወደ አሸናፊነት ነው የሚመለሰው። ስንጀምር አካባቢ በተከታታይ ወደ ሦስት ጨዋታ ከሜዳችን ውጭ መጫወታችን እጅግ በጣም ጎድቶናል።

በመጀመርያ አካባቢ ውጤት ያጣንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ የተከላካይ ስፍራችን ብዙ ስህተት እየሰራ ነበር። ይህም ግቦችን እንድናስተናግድ ዳርጎናል። ሁለተኛው ደግሞ እኔ የያዝኳቸው ተጫዋቾች ወጣቶች እንደመሆናቸው ከሜዳ ውጭ ስንጫወት ደጋፊው ሲጮህ ጫና የመቋቋም አቅማቸው ልምድ ካላቸው ተጨዋቾች አንፃር ዝቅተኛ ስለሆነ ስህተት ይሰሩ ነበር። እሱንም በሚገባ ተነጋግረን ፈትተን ክለባችን በምንፈልገው መንገዱ እያስኬድን ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ ከደረጃ ፊት ለፊት አልራቅንም፤ ቢበዛ አራተኛ ነው። ይህ ደግሞ የቡድናችን ጠንካራ ጎኑ ነው። በቀጣይ ዓመት ደግሞ ተጫዋቾቼ ወደምፈልገው መንገድ ይመጡልኛል። እኔም በመጀመሪያ ዓመት እጅግ በርካታ ልምዶችን አግንቼበታለሁ። ከወጣት ተጫዋቾች ጋር መስራት ከባድ ነው። እነሱን ማሳመን፤ ለምሳሌ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ሲቀመጥ ልትነግረው ይገባል። ለምን እንደተቀመጠ ነግረህ ስታስቀምጠው የቡድንህን መንፈስ ከፍ ያደርግልሀል። ወጣቶች ላይ ስትሰራ እኚህን ነገሮች ማወቅ አለብህ። ብዙ ነገርንም ተምሬበታለሁ፡፡

ቡድንህ አሰላለፍ እና አቀራረቡ ተገማች ነው ይባላል። ብዙውን ጊዜ ወደ አዲስ ግደይ ስለሚያደላም ቡድኖች በቀላሉ የትኩረት ማዕከላቸውን ወደ እሱ ያደርጉ ነበር። ይህን እንዴት ትመለከተዋለህ?

እውነት ነው፤ መጀመሪያ ስንጀምር አካባቢ ኳሶች ሁሉ አዲስ ነበር የሚሄዱት። አንደኛ የአዲስ አጨዋወት ያስገድድሀል፤ ተጫዋቾቹ ወደ እሱ ተስበው ይጫወቱ ነበር፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አዲስን በቃ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ እንዲጨርስ ስለሚፈልጉ ተጫዋቾቹ ኳሶቹን ወደ እሱ ነበር ሲጥሉ የነበሩት እና ይህ ደግሞ ክለባችንን ይጎዳው ነበር። ከዛ በኋላ በቀጥታ ወደ ልምምድ ነው የገባነው። እንዴት ወደ ሁለቱም ከዛ ወደ ሶስቱም አቅጣጫ ኳሶችን መጫወት እንደምንችል ሰርተናል። አሁን ከፊት ያሉት አጥቂዎች አዲስ ግደይ፣ ይገዙ ቦጋለ፣ ሐብታሙ ገዛኸኝን ጥምረት አምጥተን በጣም ውጤታማ መሆን ችለናል። ሐብታሙም አዲስም እያገቡልን ነው። ይህንን ያደረግነውም ሰርተንበት ነው።

እውነት ለመናገር ከዛ በኋላ በደንብ ነው ያወራነው። ምክንያቱም ቡድናችን ሲያሸንፍ ነው አዲስ ግደይ ስሙ የሚገነው፤ ኮከብ ግብ አግቢም የሚሆነው። ወደ አዲስ ብቻ ምናደርገው ከሆነ ቡድናችን ይገመታል። በሁለቱም አቅጣጫ የምንሄድ ከሆነ ግን ተጠቃሚው ክለቡ ነው። እኛም ተጫዋቾቹም እንጠቀማለን። ሐብታሙ በጣም አቅም ያለው ተጫዋች ነው፤ የአዲስም የሚታወቅ ነው፤ ወጣቱ ይገዙም በጣም ተቀናጅቷል።

የፊት አጥቂ ላይ የሚሰለፉት ተጫዋቾች መሐመድ፣ ይገዙ እና ፀጋዬ እምብዛም ጎል አያስቆጥሩም…

መሐመድ ናስር ልምድ ያለው ተጫዋች ነው። እንዴት ግብ ማስቆጠር እንዳለበት በሚገባ ያውቀዋል። ነገር ግን በጉዳት ምክንያት እየተጠቀምንበት አልነበረም። አሁን በብዛት ተሰልፎ እየተጫወተ ያለው ይገዙ ቦጋለ ታዳጊ ነው። እጅግ በጣም ከፍተኛ እንቅስቃሴን ነው የሚያደርገው የ። ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ይሰጣል፣ ወደ ጎል ቶሎ ቶሎ ይደርሳል። ያለመጠቀም ችግር ብቻ ነው የሚታይበት። እሱን እየበሰለ ሲመጣ ያስተካክለዋል። እነ ሐብታሙ እና አዲስ እንደበፊቱ መስመር ላይ ቆመው መጫወት ብቻ ሳይሆን ቦታ ይቀያየራሉ። የይገዙን ሚና ሐብታሙ ገብቶ ሊወጣው ይችላል። ለምሳሌ በመቐለ ጨዋታ ሐብታሙ የፊት አጥቂ ሆኖ ነው ግብ ያስቆጠረው፤ አዲስም በተመሳሳይ። እንደ ሶስቱ የሊቨርፑል ተጫዋቾች ግብ ያገባሉ ቦታም ይቀያየራሉ፡፡ በ9 ቁጥር ቦታ ከሚሰለፉ አጥቂዎች እውነት ነው የሚጠበቀውን አላገኘንም። ወደፊት ለማስተካከል እንሞክራለን። አጥቂ ጎል ማግባት ወይም ለጎል ምክንያት መሆን አለበት።

ሲዳማ ቡና መቐለን ካሸነፈ በኃላ በይበልጥ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ገብቷል። አሁን ደግሞ በእኩል ነጥብ እየተፎካከረ ነው…

የኛ እቅድ ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች እያሸነፍን ከዛ ቦታ ላይ ያለመራቅ ነው። ከፊትህ ያለውን ጨዋታ ስታሸንፍ አትርቅም። እኛ መቐለ ወይም ፋሲል ነጥብ ይጣል አይጣል የሚል ነገር በተጫዋቾቼም እኔ ጋርም የለም። ምክንያቱም ከፊት ለፊት ያሉትን ጨዋታዎች እያሸነፍክ ስትሄድ የምትፈልገውን ነገር ታገኛለህ። ዋንጫውን ብቻ ማሰብ ስራህን ያስረሳሀል። ጨዋታን እያሸንፍክ ስትሄድ ያኔ የምትፈልገውን ታገኘዋለህ። ለዋንጫ ነው የምንጫወተው፤ ለዋንጫ የምትጫወት ከሆነ እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ አለብህ። ለዚህ ደግሞ በምንም ጨዋታ ተዘጋጅተህ ነው መሄድ ያለብህ። አሸነፈን ቡድናችንን የዋንጫ ተፎካካሪ እናደርገዋለን ብዬ አስባለሁ።

ዘንድሮ በተለየ መልኩ የክለባችሁ ደጋፊዎች በጣም ክለቡን እያበረታቱ ይገኛሉ። እንዴት አገኘኸው?

እውነት ለመናገር ደጋፊዎቻችን የክለባችን አቅም ናቸው። በተለይ የደጋፊ ማኅበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ ለቡድኑ የሚያሳዩት ፍቅር እጅግ በጣም ከፍተኛ ፍቅር ነው። ሀዋሳ ላይ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች በተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ መነሳሳትን የሚፈጥሩልን ደጋፊዎቻችን ናቸው። ከዚህ በላይ ከተሰራበት የሲዳማ ቡና ደጋፊ ለወደፊቱ ለክለቡ ትልቅ አቅም ነው። ደጋፊዎቻችንን ከልብ ማመስገን እፈልጋለው። ምክንያቱም እዚ እንድንደርስ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል። ውጤት ሲጠፋ የደጋፊው ማኅበር መጥቶ ከኛ ጋር ይነጋገራል። ችግሮች በመፍታት ክለባችን ውጤታም እንዲሆን የማያደርገው ነገር የለም። ለነሱም ስንል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። በዚው ቀጥሉ አጠገባችን ሁናቹችሁ አበረታቱን እላለው። እስከምንችለው ድረስ መስዋዕትነትን ከፍለን እስከ ዋንጫውም ቢሆን ክለባችንን ውጤታማ እናደርጋለን።

የቤተሰብ ሁኔታህ ምን ይመስላል?

ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። በትዳሬም በጣም ደስተኛ ነኝ። ባለቤቴ ለስራዬ በጣም አጋዥ ነች። እሷም ወጣት ስለሆነች ትረዳኛለች። ሜዳም አትቀርም፤ እየመጣች ትመለከታለች። ያለውን ነገር ጫናውን ሁሉ ከኔ እኩል ነው የምትጋራው። ቤት ውስጥ ጠንካራ ሰው ሲኖር አንተም ጠንካራ ትሆናለህ። ምክንያቱም እዛ ጋር ያለውን ነገር የምታስብ ከሆነ ስራህ ሁሉ ይበላሻል። በዛ የተነሳ በጣም ደስተኛም ነኝ። ደክሞኝ እና ተጨንቄ ቤት ስሄድ ሠላም የማገኘው በባለቤቴ እና ልጆቼ ነው።

ላንተ አርዓያህ ማነው?

ከሀገር ውስጥ በጣም የምወዳቸው ብዙ አሰልጣኞች ስላሉ መለየት ይከብዳል። ከብዙዎቹ ጋር እግባባለሁ። ተጫዋች እያለሁም ሆነ አሰልጣኝ ሆኜ ከሁሉም ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ለኔ ግን የውበቱ አባተ ፍልስፍና ደስ ይለኛል። ምክንያቱም በእውቀት የተመሰረተ ነገር ነው የሚያደርገው። የሱ አጨዋወት ኳስ መስርቶ የሚጫወት እና ለተመልካችም አዝናኝ ኳስ ነው። ያ የኔ ፍላጎቴም ስለነበር ውስጤም አለ። የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በተፈጥሮ ችግር የለብንም። ስለዚህ በደንብ መስራት ያለብን እዚህ ላይ ነው፡፡ ውበቱ ጋር ደግሞ መሠረቱ ስላለ የሱ ተጫዋቾች ኳስ ይዘው መጫወት ስለሚችሉ ብሔራዊ ቡድን ቢሄዱም አይቸገሩም። ከውጭ ምንም ጥያቄ የለውም ፔፕ ጓርዲዮላ ነው። አሁን ውጤታማ ስለሆነ አይደለም ባርሴሎናም፣ ሙኒክም፣ ሲቲም ሲመጣ አጨዋወቱን አልቀየረም። ክለብ ቢቀየርም እኔ ለምፈልገው አጨዋወት ስለሚመች የፔፕ ጓርድዮላ አድናቂ ነኝ።

በስተመጨረሻ ፕሪምየር ሊጉ ባንተ ዕይታ ምን ይመስላል?

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተቀየረ ነው ያለው። በፊት አንድ እና ሁለት ክለቦች ብቻ ነበሩ ለዋንጫ የሚፎካከሩት። አሁን ግን የክልል ክለቦች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ መጥተዋል። ይህ በፊት ያልነበረ ነገር ነው። ኳሱ በየቦታው ተወዳጅ እየሆነ ነው። ሊጉ በራሱ አሁን ጠንካራ እየሆነ ያለ ይመስለኛል። ግን በብሔራዊ ቡድን ደረጃም እንደዛ መስራት አለብን። ይህ ደግሞ የኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ኃላፊነት ብቻ አይደለም፤ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። የአስራ ስድስቱም ፕሪምየር ሊግ ብቻም አይደለም። ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን እንዲሆን ከተፈለገ ከፕሪምየር ሊግ አንስቶ እስከ ታችኛው የሊግ እርከን ያለነው አሰልጣኞች አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው። ምክንያቱም የነዚህ አስተዋፅኦ ድምር ውጤት ነው ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የሚገነባው። ሁላችንም ይህንን መሰረት አድርገን ለሀገራችን የሚጠቅም ነገር ብንሰራ ወደፊት የተሻለ ቦታ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡