ሳላዲን እና ኤምሲ አልጀር የተለያዩበት ምክንያት ይፋ ሆነ

ሳላዲን ሰዒድ ኤምሲ አልጀርን አስቀድሞ መልቀቅ ፈልጎ እንደነበር ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረቻቸው ሁለት የአልጄሪያ ጋዜጠኞች ገልፀዋል፡፡ ጋዜጠኞቹ ሳላ ከአልጀርሱ ክለብ የተለያየው በቂ የመጫወት ዕድል ስለተነፈገው እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ 

ለአልጄሪያው የእግርኳስ ድረገፅ dzfoot.com በጋዜጠኛነት የሚያገለግለው ዋሊድ ባይካ እንደገለፀው ከሆነ ሳላ በአልጀርስ ደርቢ ኤምሲ አልጀር ከዩኤስኤም አልጀር ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ አለመግባቱ ከክለቡ እንዲለቅ አስገድዶታል፡፡ “ሳላዲን በአልጀርስ ደርቢ ተቀይሮ አለመግባቱ በጣም አበሳጭቶታል፡፡ የመቀመጫ ወንበር እስከመምታት ደርሶ ነበር፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለክለቡ ፕሬዝደንት የልቀቁኝ ድብዳቤ አስገብቶ ነበር፡፡” ሲል ሃሳቡን ይሰጣል፡፡

ለኤምሲ አልጀር ቅርብ እንደሆነ ለሚነገርለት mouloudia.org የሚሰራው ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገው ሌላው አልጀሪያዊ ጋዜጠኛ በበኩሉ ሳላ በአልጀርስ ደርቢ ያሳየው ያልተገባ ባህሪ ከክለቡ እንዲለቅ ምክንያት ሆኗል ይላል፡፡ “የሳላ ውል በስምምነት ነው የፈረሰው፡፡ በተጫዋቹ ላይ በአልጀርስ ደርቢ ያልተገቡ ባህሪያት መታየታቸው እንዲሁም በቂ የመሰለፍ ዕድል አለማግኘቱ ከክለቡ እንዲለያይ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ከክለቡ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ሳይጎዳ ተጎዳው ማለቱም ከክለቡ ጋር ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ አድርጎት ነበር፡፡ በርግጥ እውነት ይሁን ሃሰት አናውቅም፡፡ ሳላ ትልቅ ተጫዋች ነው ነገር ግን የፈረመበት ግዜ ትክክል አልነበረም፡፡ ክለቡ በጥሩ ሁኔታ ላይ እያለ ቢፈርም ኖሮ ከሱ የተሻለ ነገር እናይ ነበር፡፡”

ሳላዲን ከወዲሁ ለዩኤስኤም አልጀር ጋር ለዝውውር ስሙ እየተነሳ ነው፡፡ “ወደ ዩኤስኤም አልጀር ሊዘዋወር ነው የሚሉ ያልተረጋገጡ ወሬዎች በስፋት ይራገባሉ፡፡ በርግጥ የአልጄሪያ ሊግ ክለቦች የውጭ ሃገር ተጫዋቾችን እንዳያስፈርሙ የተከለከሉ ቢሆንም አንዳንድ ክለቦች ግን ከህግ በላይ ስለሆኑ ሳላዲን ወደ ሌላ የአልጄሪያ ክለብ የመጓዝ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡” አልጄሪያ የውጭ ሃገራት ተጫዋቾች በሃገሯ ባሉ ክለቦች እንዳያስፈርሙ በመስከረም ወር ነበር ህግ ያወጣችው፡፡

ሳላዲን ዋዲ ደግላን ከለቀቀ በኃላ በግብፁ ሃያል ክለብ በአል አሃሊ እና ኤምሲ አልጀር ያልተሳካ የዓመት ከስድስት ወር ቆይታ ነበረው፡፡

ያጋሩ