ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ሲዳማ ቡና

መከላከያ እና ሲዳማን በሚያገናኘው የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ እና ታች ያሉት ፉክክሮች ላይ ለውጦችን የማስመልከት ዕድል ያለው ይህ ጨዋታ ነገ 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይከናወናል። እጅግ ወሳኝ በነበረው የሳምንቱ የሽረ ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገደው መከላከያ ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቹ ሁለት ነጥቦችን ብቻ በማሳካቱ የነገውን ከባድ ፈተና በድል መወጣት ብቸኛው አማራጩ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የቅርብ ተከታዮቹ ውጤት ከቀናቸው ግን መከላከያ ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ አይቀርም። አራት ተከታታይ ድሎችን ያጣጣሙት ሲዳማዎች ደግሞ በዋንጫ ፉክክሩ ከመቀጠል ባለፈም ቢያንስ ፋሲል እና መቐለ ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ ሊጉን ለመምራት የሚያስችሏቸውን ሦስት ነጥቦች ፍለጋ ጦሩን የሚገጥሙ ይሆናል።

የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት መከላከያዎች በአማካይ ክፍላቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ላይ ተመስርተው ጨዋታውን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ነገር ግን የሲዳማ የመልሶ ማጥቃት በትር እንዳያርፍባቸው ከኋላ ጥንቃቄ ማድረጋቸው የማይቀር ነው። በጨዋታው መሀል ላይ ለተከላካይ ክፍሉ ጥሩ ሽፋን የሚሰጡ ሁለት አማካዮችን የሚይዘው ተጋጣሚያቸውን አልፈው ለብቸኛው አጥቂያቸው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ደግሞ ሌላኛው ፈተናቸው ይሆናል። መከላከያ እስካሁን በመጣበት መንገድ በሜዳው አጋማሽ ኳስ በሚነጠቅባቸው ወቅቶች በፍጥነት ማገገም ካልቻለ ግን ጨዋታው ሊከብድበት መቻሉ ዕሙን ነው። የአሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን ቡድን የመስመር ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝን ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት መልስ በማግኘት በነገው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ የሆነውን የቀኝ መስመሩን መከላከል የሚያጠናክር ሲሆን ምንይሉ ወንድሙ ግን አሁንም በጉዳት የሌለው ብቸኛው ተጫዋቹ ሆኗል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከመዲናዋ በድል የተመለሱት ሲዳማዎች ነገም ጥንቃቄ ያልተለየው በዛው ልክ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በንቃት የሚጠብቅ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። ከኳስ ውጪ ወደ ተከላካይ ክፍሉ ቀርቦ እንደሚንቀሳቀስ የሚጠበቀው በዳዊት ተፈራ ወቅታዊ ድንቅ ብቃት የሚመራው የአማካይ ክፍልም ከኳስ ጋር ሲገናኝ የመስመር አጥቂዎቹ በፍጥነት ወደ ጦሩ ሳጥን የሚገቡበትን አማራጭ እንደሚፈጥር ይገመታል። ከዚህ በላፈም በተሻለ ሁኔታ ኳስ ሊይዝ የሚችለውን የተጋጣሚውን ቅብብሎች በራሱ ሜዳ ላይ በቶሎ ማቋረጥ እና ራሱን ለመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች ዝግጁ ማድረግ ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን ይጠበቃል። ሲዳማ ቡና የፊት አጥቂው መሀመድ ናስርን እና የመስመር ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞንን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን በደቡብ ፖሊሱ ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የወጣው ወንድሜነህ አይናለምም ወደ ሜዳ አይመለስም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች 

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 19 የእርስ በርስ ግንኙነት አድርገዋል። ሰባቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጣት ሲጠናቀቁ ሲዳማ ሰባት ፤ መከላከያ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ሲዳማ 17 መከላከያ ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ 14 ጨዋታዎችን ያከናወነው መከላከያ ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው አራቴ ነጥብ ተጋርቶ በሰባት ጨዋታዎች ተሸንፏል

– ሲዳማ ቡና ከድቻ ጋር በገለልተኛ ሜዳ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ሳይጨምር ከሜዳው ውጪ 10 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ሁለት ጊዜ ድል አድርጓል ። ከዚህ ውጪ ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋራ አምስት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው 15 ጨዋታዎች 47 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ 2 የቀይ ካርድ እና 3 የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-2-3-1)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ታፈሰ ሰረካ

አማኑኤል ተሾመ – ቴዎድሮስ ታፈሰ 

ተመስገን ገብረኪዳን – ዳዊት እስጢፋኖስ – ፍሬው ሰለሞን

 ፍቃዱ ዓለሙ
                                   

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ግሩም አሰፋ – ሰንደይ ሙቱኩ

ግርማ በቀለ – ዮሴፍ ዮሃንስ – ዳዊት ተፈራ

ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ – አዲስ ግደይ