ሀዋሳ እና መቐለ ላይ የሚደረጉትን የነገ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።
ደቡብ ፖሊስ ከ ሀዋሳ ከተማ
ሁለቱን የሀዋሳ ክለቦች እርስ በርስ የሚያገናኘው ጨዋታ ትርጉም ለደቡብ ፖሊስ ያደላ ነው። ሳምንት በሌላው የከተማቸው ክለብ ሲዳማ ቡና ለመሸነፍ የተገደዱት ደቡብ ፖሊሶች ከሽረ እና መከላከያ በአንድ ነጥብ ብቻ አንሰው 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ነገ እጅግ አስፈላጊያቸው የሆነውን ድል ማሳካት ከቻሉም ከወራጅ ቀጠናው ለጊዜውም ቢሆን የመውጣት ዕድል ይገጥማቸዋል። ደቡብ ፖሊሶች በወሳኙ ጨዋታ ከጉዳት መልስ የብርሀኑ በቀለ እና ኤርሚያስ በላይን ግልጋሎት የሚያገኙ ይሆናል። በሰንጠረዡ አጋማሽ የተደላደሉት ሀዋሳዎች በበኩላቸው ቅጣት አስተላልፈውበት የነበረው ታፈሰ ሰለሞንን ወደ ሜዳ የመመለሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ከመሆኑ ባሻገር ገብረመስቀል ዱባለን በጉዳት ሲያጡ መሳይ ጳውሎስን ከ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት ቸርነት አውሽ እና ሄኖክ ድልቢን ደግሞ ከመጠነኛ ጉዳት መልስ እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ክለቦች በ2001 ፣ 2002 እና የዘንድሮ ውድድር ዓመታት ከተጋናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች የመጀመሪያ ሦስቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሀዋሳ የመጨረሻ ሁለት ግንኙነቶቻቸውን በ2-0 እና 3-2 ውጤቶች አሸንፏል። በድምሩም ሀዋሳ ከተማ ሰባት ደቡብ ፖሊስ ደግሞ አራት ግቦችን አስቆጥረዋል።
– ሀዋሳ ላይ 14 ጨዋታዎችን ያደረገው ደቡብ ፖሊስ አራት ጊዜ ድል አድርጎ አንዴ ነጥብ ሲጋራ በቀሪዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች ግን ምንም ነጥብ ማሳካት አልቻለም።
– በተመሳሳይ በሀዋሳ 12 ጨዋታዎችን ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ስድስቱን አሸንፈው በአራቱ ሲሸነፉ በቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ሀዋሳ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው ማሸነፍ የቻለውም 12ኛው ሳምንት ላይ ያገኘውን የነገ ተጋጣሚው ደቡብ ፖሊስን ነበር።
ዳኛ
– ጨዋታውን የሚመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ እስካሁን 13 ጨዋታዎችን ዳኝቷል። በጨዋታዎቹ 45 የቢጫ ካርዶችን መዞ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችንም ሰጥቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)
መክብብ ደገፉ
አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – ዘሪሁን አንሼቦ – ዘነበ ከድር
ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ኪዳኔ አሰፋ
የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – ብሩክ ኤልያስ
ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)
ሶሆሆ ሜንሳህ
አዲስዓለም ተስፋዬ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ
ያኦ ኦሊቨር – አክሊሉ ተፈራ – ሄኖክ ድልቢ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ደስታ ዮሀንስ
አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ
ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ አዳማ ከተማ
በሦስት ነጥቦች ልዩነት 7ኛ እና 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎ እና አዳማ በቀሪዎቹ ሳምንታት የተሻለ ደረጃ ይዞ ዓመቱን ከመጨረስ ያለፈ ግብ ያላቸው አይመስልም። በመሆኑም ከጫና ነፃ የሆነ ፉክክር ያለበት እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጨዋች የሌለ ሲሆን በቅርብ ጨዋታዎች ከቁልፍ ተጫዋቾቻቸው ይልቅ የወጣት እና አዲስ ፈራሚዎቻቸውን ድርሻ እየጎሉ የመጡት አዳማ ከተማዎች ግን አንዳርጋቸው ይላቅ ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና ምኞት ደበበን በጉዳት ሳቢያ የማይጠቀሙ ይሆናል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– እስካሁን በተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜም አቻ ያልወጡ ሲሆን አዳማ ሁለቴ ወልዋሎ ደግሞ አንዴ ድል አድርገዋል። አዳማ አራት ጊዜ ወልዋሎ ፤ አንድ ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
– ትግራይ ስታድየም ላይ 14 ጨዋታዎችን ያደረገው ወልዋሎ አምስቴ ድል ሲቀናው ሦስት ሽንፈት እና ስድስት የአቻ ውጤቶች ገጥመውታል።
– አዳማ ከተማ 13 ጊዜ ከሜዳው ሲወጣ መከላከያን ከረታበት ጨዋታ ውጪ ሰባት ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ዳኛ
– በመሀል ዳኝነት በተመደበባቸው 12 ጨዋታዎችን 51 የቢጫ ካርዶችን እንዲሁም አራት ቀጥታ ቀይ ካርዶችን የመዘዘው እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ሮበርት ኦዶንካራ
ሱለይማን ሰሚድ – ተስፋዬ በቀለ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ
ብሩክ ቃልቦሬ – አዲስ ህንፃ
ኤፍሬም ዘካርያስ – ፉዓድ ፈረጃ – ዱላ ሙላቱ
ቡልቻ ሹራ
ወልዋሎ ዓ/ዩ (4-2-3-1)
ዓብዱልአዚዝ ኬይታ
እንየው ካሳሁን – በረከት አማረ – ደስታ ደሙ – ብርሃኑ ቦጋለ
አማኑኤል ጎበና – አፈወርቅ ኃይሉ
ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ዓብዱራሕማን ፉሴይኒ – ኤፍሬም አሻሞ
ሬችሞንድ አዶንጎ