የነገ ተጋጣሚው ጅማ አባ ጅፋር ወደ ሶዶ ባለማምራቱ ወላይታ ድቻ ዳግመኛ በፎርፌ ውጤት የማግኘቱ ነገር የማይቀር መስሏል።
በ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወላይታ ድቻ እና በጅማ አባ ጅፋር መካከል የሚደረገው ጨዋታ ነገ 9:00 ሰዓት በሶዶ ስታድየም እንዲደረግ መርሐግብር የወጣለት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች ባልተከፈላቸው የሦስት ወር ደምወዝ ምክንያት ያሳለፍነውን ሳምንት ሙሉ ልምምድ ሳያከናውኑ መቅረታቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ ዋንጫ በተመሳሳይ ከድቻ የነበራቸውን ጨዋታ አለመድረጋቸውን ተከትሎ ነገም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ሲጠበቅ ነበር።
በጉዳዩ ዙሪያ የክለቡን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የተጫዋቾቹን ደምወዝ የመንግስት የበጀት ክፍያ ሂደት ሊያዘገየው እንደቻለ እና ደምወዝን ጨምሮ ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን ለመሸፈን በሂደት ላይ መሆናቸውን የሶከር ኢትዮጵያ ምንጮች ይጠቁማሉ። ነገር ግን ጉዳዩ እስካሁን መፍትሄ ባለማግኘቱ እና ተጨዋቾቹ ወደ ሶዶ አለማምራታቸው ጨዋታው በወላይታ ድቻ የፎርፌ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ይጠቁማል።