አመሻሹ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የተከናወነው ድንቅ ጨዋታ መከላከያን ከሙሉ ብልጫ ጋር ባለድል ሲያደርግ ፤ ሲዳማ ቢያንስ ለ24 ሰዓታት ሊጉን የመምራት ዕድሉን አምክኗል።
ሣምንት ሽረ ላይ ሽንፈት ከገጠመው ቡድኑ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረገው መከላከያ በሙሉቀን ደሳለኝ ፣ አማኑኤል ተሾመ እና ሳሙኤል ታዬ ምትክ ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የተመለሰው ሽመልስ ተገኝ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ፍፁም ገብረማርያምን በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ አካቷል። ሲዳማ ቡና በበኩሉ ደቡብ ፖሊስን በረታበት ጨዋታ ጉዳት የገጠመው የወንድሜነህ ዓይናለም እና የይገዙ ቦጋለን ቦታ በዳዊት ተፈራ እና ጫላ ተሺታ በመሸፈን ጨዋታውን ጀምሯል።
በሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሽልማት መርሐግብር ምክንያት 25 ደቂቃዎችን የዘገየው ጨዋታው ከፍ ባለ ፍጥነት ጀምሮ ሳይቀዘቅዝ የተቋጨ ነበር። ሲዳማዎች ጫላ ተሺታ ወደ ተሰለፈበት ቀኝ መስመር በሚልኳቸው ኳሶች እና መከላከያዎች ከወትሮው በተለየ የተዋጣለት አደረጃጀት ኳሶችን በፍጥነት በማስጣል በሚያደርጉት ማጥቃት ግለቱ ከፍ ያለው ጨዋታ ግብ ለማስተናገድም እምብዛም አልቆየም። 9ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን የቅጣት ምት ፍቅሩ ወዴሳ በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ኳስ ከእጁ ስታመልጠው አግኝቶ ፍፁም ገብረማርያም መከላከያን መሪ አድርጓል።
ከግቡ በኋላ ይበልጥ ትኩረታቸው ከፍ ብሎ የታዩት መከላከያዎች በተጋጣሚያቸው ላይ ሰፊ ብልጫ ወስደዋል። ኳስ ወደ ሲዳማ ሦስት አጥቂዎች ከመድረሷ በፊት በቶሎ በማቋረጥ በቀኝ መስመር ወደ ፍፁም አመዝነው ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ባደረጉት ሙከራም አዲሱ ተሰፋዬ ሳጥኑ መግቢያ ላይ ከፍፁም የተቀበለውን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። የጦሩ ተጫዋቾች ታታሪነታቸው ከፍ ባለባቸው በነዚህ ደቂቃዎች ሲዳማዎች ደግሞ እጅግ ወርደው ታይተዋል። ከባለሜዳዎቹ አጥቂዎች ከሚደርስበት ጫና ኳስ ለመጀመር የተቸገረው የኋላ መስመራቸው እና በቶሎ ኳስ የሚነጠቀው የአማካይ ክፍላቸው ከአጥቂዎቹ ጋር ተለያይቶም ቆይቷል። ቡድኑ ይታይበት የነበረው አለመረጋጋትም በተከታታይ ተጨማሪ ግቦች እንዲቆጠርበት ምክንያት ሆኗል። በዚህም በ23ኛው ደቂቃ ፈቱዲን ጀማል ግማሽ ጨረቃው ላይ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ በቀጥታ በመምታት ሲያስቆጥር ከአንድ ደቂቃ በኋላ ፍሬው ሰለሞን የሲዳማው ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ ከግብ ክልሉ መውጣቱን አይቶ ወደ መሀል ሜዳው ከቀረበ ቦታ ላይ በረጅሙ የመታውም ኳስ ከመረብ አርፎ ውጤቱ 3-0 ሆኗል።
ከዚህም በኋላም ከተጨዋቾች የግል ብቃት መጉላት ባለፈ የመከላከያ እንደቡድን ክፍተቶችን በመሸፈን እና ከሚነጠቁ ኳሶች በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ መሞከር በስፋት ይስተዋል ነበር። ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ተጎድቶ ጨዋታው ለረጅም ደቂቃዎች ተቋርጦ 35ኛው ደቂቃ ላይ ከጀመረ በኋላ ግን የባለሜዳዎቹ የበላይነት ቀነስ ብሎ ታይቷል። ወደ መረጋጋት ለመመለስ ብዙ ደቂቃ የወሰደባቸው ሲዳማዎች አዲስ ግደይን ወደ መሀል አጥቂነት በማምጣት እንዲሁም አበባየው ዮሀንስን በዳዊት ተፈራ ቀይረው በማስገባት ወደ ጨዋታው ምት ለመግባት ሞክረዋል። የተሻለ ጫና በፈጠሩባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎችም አደገኞቹን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች መፍጠራቸው አልቀረም። 39ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከጫላ ተሺታ በተቀበለው ኳስ ተቀይሮ ከገባው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር ተገናኝቶ ሲመለስበት 45ኛው ደቂቃ ላይም ከጫላ የተነሳን ኳስ ሀብታሙ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ነገር ግን ሰከንዶች ሲቀሩ የሀብታሙ ገዛኸኝ ወደ ግራ ያደላ የርቀት ቅጣት ምት ተጨርፎ መረብ ላይ በማረፉ ጨዋታው በ3-1 ውጤት ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ሁለተኛውን አጋማሽ መከላከያዎች እንደመጀመሪያው ሁሉ በማጥቃት ላይ ተመስርተው ሲጀምሩት ልዩነቱን የማጥበብ ግዴታ ውስጥ የገቡት ሲዳማዎችም ተመሳሳይ ምላሽን ሰጥተዋል። ጨዋታውም በቅርብ ጊዜያት በአዲስ አበባ ስታድየም ከታዩ ጨዋታዎች በተለየ በግቦች እና በሙከራዎች የታጀበ ሆኖ ቀጥሏል። ጠንካራ ጎናቸው የሆነውን የመስመር ጥቃት ለማጠናከር ይገዙ ቦጋለን ቀይረው ያስገቡት ሲዳማዎች ተጫዋቹ 54ኛው ደቂቃ ላይ ባሻገረው ኳስ የመጀመሪያውን ከባድ ሙከራ አድርገዋል። ኳሱን አዲስ ሲጨርፍለት ግሩም አሰፋ አግኝቶ አክርሮ መትቶ ለጥቂት ነበር ወደ ውጪ የወጣበት። በተመሳሳይ አኳኋን ከኳስ ውጪ ጫናን በማሳደር እንዲሁም በመስመር ተከላካዮቻቸው ሽመልስ ተገኝ እና ታፈሰ ሰረካ ልዩ ብቃት የሲዳማ የሦስትዮሽ አጥቂ መስመር ጋር ኳስ እንዳይደርስ በትጋት መጫወታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በ58ኛው ደቂቃ ፍፁም ሳጥን ውስጥ ተከላካዮችን አሸማቆ ከቅርብ ርቀት ባደረገው ሙከራ የግብ ልዩነቱን ለማስፋት ቢሞክሩም ፍቅሩ አድኖባቸዋል። ሆኖም 61ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ ሆኖ ያመሸው ፍፁም ተከላካዮችን አዘናግቶ ያሳለፈለትን ኳስ ታፈሰ ሰረካ ከግራ በኩል ነፃ ሆኖ ወደ ውስጥ ሲያሻግር ፍቃዱ ዓለሙ በግንባሩ አስቆጥሮ የባለሜዳዎቹን መሪነት ከፍ አድርጓል።
ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማዎች ባላቸው ኃይል ሁሉ ግብ ለማግኘት የተንቀሳቀሱባቸው ነበሩ። ነገር ግን ወደ ግራ መስመር አጥቂነቱ በተመለሰው አዲስ ግደይ ላይ ብቻ ትከረት ማድረጋቸው እና የይድነቃቸውን አስገራሚ የግብ ጠባቂነት ብቃት ማሸነፍ አለመቻላቸው ግብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። አዲስ 67ኛው ደቂቃ ላይ ከአበባየው በረጅሙ ያደረሰውን ኳስ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ገፎት በመግባት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ግርማ ከመሀል ሜዳው ጠጋ ብሎ በድንገት አክርሮ የመታው ኳስ ከመረብ ሊያርፍ ተቃርቦ ነበር። በዛው ደቂቃ አበባየው ሳጥን ውስጥ ጠንከር ባለ ምት ያደረገው ሙከራም ግብ ለመሆን የሚችል ነበር ፤ ሦስቱም ኳሶች ግን ከመረብ ያላረፉት በይደነቃቸው ኪዳኔ ልዩ ብቃት ነበር። ተጋጣሚያቸውን ሁለት ቦታ መስበር የቻሉት መከላከያዎችም ወደ ሲዳማ የግብ ክልል የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አልነበሩም በተለይም 75ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተጨረፈ ኳስ ዳዊት እስጢፋኖስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ መትቶ ወደ ላይ የተነሳበት እና በ81ኛው ደቂቃ እዛው ቦታ ላይ በድጋሜ ዳዊት በድንቅ ሁኔታ የተቆጣጠረውን ኳስ ተከላካዮችን አልፎ ቢሞክርም ለጥቂት በቋሚው ጎን የወጣበት የሚጠቀሱ ነበሩ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማዎች ጫናቸው ሲበረታ በ86ኛው ደቂቃ የአበባየውን የቅርብ ሙከራ ታፈሰ ሰረካ ከመስመር ላይ በግንባር ሲያወጣው ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ግርማ በቀለ ከቅርብ ርቀት ያገኘውን አጋጣሚ በማይታመን መልኩ ወደ ላይ ልኮታል። ሌላኛው የግርማ ከባድ የርቀት ሙከራ እንዲሁም 89ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ሀሲሳ ከግራ አሻምቶት አዲስ በግንባሩ የሞከረው ኳስ በይድነቃቸው ጥረት ድነዋል። እንግዶቹ በዚህ መልኩ ጥረታቸው ሳይሰምርም ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል። በውጤቱ ሲዳማ ቡና ሊጉን ለብቻው መምራት የሚችልበትን ዕድል ሲያመክን መከላከያ ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ በማለት ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ውስጥ ትልቅ እርምጃ መራመድ ችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡