የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ 1-1 አዳማ ከተማ

መቐለ ላይ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ለደረጃ ትኩረት ሳንሰጥ ለወጣቶቹ ትኩረት እንሰጣለን” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በቡድን ደረጃ በኅብረት በማጥቃት እና በመከላከል እኛ የተሻልን ነበርን። እነሱ ደግሞ በየቦታቸው ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች አሏቸው። መጨረስ ላይ እየተቸገርን ነው። በሁለተኛው አጋማሽም ጉጉት ስለነበረ ስዓት ሊያልቅ ነው ብለን ከኃላ ነቅለን ከወጣን በኃላ በመጨረሻ ሰዓት ላይ አግብተው ነበር። ሌላ መጨረስ የሚገባቸው አንድ ኳስም ነበር። ወጣት ተጫዋቾች ማሳደግ አንዱ ጥቅሙ ይሄ ነው ጉጉት ያላቸው መጫወት የሚፈልጉ ጥሩ ተስፋ ያላቸው በእንደዚ አይነት ሰዓት ገብተው ወሳኝ ነጥብ ይዘህ እንድትወጣ ይረዱሃል። በአጠቃላይ በቡድን ደረጃ እኛ የተሻልን ነበርን። በተናጠል ደሞ እነሱ የተሻኑ ነበሩ።

ቡድኑ ስላለበት የጎል ማግባት ችግር

ልንጨርስ ነው እንደዚህ እያልን። ዓመቱ ሊያልቅ ሶስት ጨዋታ ነው የቀረን። ለዚህ ነው በኅብረት የምንጫወተው። ማን እንደሚያገባ አናውቅም። ምክንያቱ ደግሞ የቡድን ስራ ስለምንሰራ ነው። በአንድ እና ሁለት በተጫዋቾች አንተማመንም፤ የምንተማመነው በሁሉንም ነው። በአንዳንድ ጨዋታዎች ይዘውህ የሚወጡ አጥቂዎች ያስፈልጉሃል፤ እነሱ ደግሞ። የሉንም ስለዚህ እንደቡድን ስራችንን መስራት አለብን። በቀጣይ ሦስት ጨዋታዎችም እንዲህ ነው የምንቀጥለው።

ለወጣቶች ተጨማሪ ዕድል በመስጠት ለቀጣዩ ዓመት የተሻለ ዝግጁ እንዲሆኑ ቀጣይ ሶስት ጨዋታዎች ላይ ወጣቶች ላይ ትኩረት እናደርጋለን።
ሲቀጥልም ለደረጃ ትኩረት ሳንሰጥ ለወጣቶቹ ትኩረት እንሰጣለን።

“ቀጣይ ሦስት ቀሪ ጨዋታዎች አሉብን። እነሱን አሸንፈን ደረጃችን ማሻሻል ነው” ደጉ ዱባም (አዳማ ከተማ – ምክታል አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው እንዳያችሁት ጥሩ ነበርን። አሸንፈን ለመሄድ ነበር የመጣነው። ያንን ለማሳካት እስከ መጨረሻው ሄደን በመጨረሻው ደቂቃ ጎል ገብቶብናል። ያው ኳስ ነው እንቀበላለን።

ከጎል በኋላ ስለነበረው እንቅስቃሴ

ከጎል በኋላ አሸንፎ ለመሄድ ከነበረው ጉጉትም አፈግፍገን ነበር። ያም ቢሆን ጎሉ የተቆጠረበት ደቂቃ ሰዓቱ ሄዷል ባይ ነኝ። እንዳሸነፍን ነው የምቆጥረው። ተጫዋቾቹ ያደረጉት እንቅስቃሴ የተሻለ ነው። ነጥቡ ይገባን ነበር።

ቀጣይ…

ቀጣይ ሶስት ቀሪ ጨዋታዎች አሉብን። እነሱን አሸንፈን ደረጃችን ማሻሻል ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡