መከላከያ ሲዳማ ቡናን በአዲስ አበባ ስታድየም አስተናግዶ 4-1 ከረታበት ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
“ቡድናችን የሚገኝበት ደረጃ የሚገባው አይደለም” በለጠ ገብረኪዳን – መከላከያ
ስለጨዋታው
“ጨዋታው ከምገልፀው ባላይ ነው። በድናችን በቅርብ ጨዋታዎች ያለው መነሳሳት በጣም ጥሩ ነው። ሽረ ላይም ስንሸነፍ በቡድኔ እንቅስቃሴ ኮርቼ ነበር ፤ ዛሬም ጥሩ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነበርኩ። አሁን ያለው የቡድኑ መንፈስ በጣም ጥሩ ነው። ተጫዋቾቼ በዚህ ጭቃ 90 ደቂቃ የተጫወቱ አይመስሉም ነበር። ቡድናችን የሚገኝበት ደረጃ የሚገባው አይደለም። ከዚህ በላይ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ እየሰራን ነው። በተጫዋቾቼ ብቃት ግን ከልብ ኮርቻለው።”
የአቤል ማሞ የጉዳት ደረጃ
“አቤል ቅድም ሲወጣ ህመም ላይ ነበር። አሁን ጨዋታው ካለቀ በኋላ ሳየው ግን ደህና ነው። ተቀይሮ የገባው ግብ ጠባቂያችን ባደረገው እንቅስቃሴም በጣም ኮርቻለው።”
ዛሬ ቡድኑ ያሳየው የተለየ መነሳሳት
“የተለየ ነገር ምንም የለም። ተጫዋቾቹ ቡድኑ አሁን ያለበት ደረጃ ከኔ በላይ ነው የሚያስጨንቃቸው ፤ አይገባቸውምም። እውነቴን ነው የምነግራችሁ ያለአሰልጣኝ መጫወት የሚችሉ ናቸው። በጣም ጥሩ ስብስብ ነው ፤ በጣም ጥሩ የኳስ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾችንም ያካተተ ነው። ዛሬ እከሌ ደካማ ነው እከሌ ጠንካራ ነው ማለት ይቸግራል። ባደረጉት ነገር ባጣም ኮርቻለው።”
” ለኛ አጨዋወት ሜዳው ምቹ አልነበርም” ዘርዓይ መሉ – ሲዳማ ቡና
ስለጨዋታው
“ዛሬ ጥሩ አልነበርንም። ጥሩ እንዳንሆን ያደረገንም ሜዳው ነው። ለኛ አጨዋወት ሜዳው ምቹ አልነበርም ፤ ስንቸገር ነበር። በዚህም ምክንያት ነጥብ ጥለናል። አሁንም ፉክክሩ ውስጥ ነው ያለነው ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ የሚታወቅ ይሆናል። በአጠቃላይ ቡድናችን ጥሩ አልነበረም ፤ መከላከያ ጥሩ ስለነበር አሸንፏል።”
ቅያሪዎች ከሜዳው አስቸጋሪነት አንፃር
“ቅያሪዎች ያደረግነውም ለዛ ነበር። ሜዳው አቅም ይጠይቃል ኳስ ይዞ ለመጫወት አስቸጋሪ ነው። እነ ዳዊት ተፈራን የቀየርነውም ከዚህ የተነሳ ነው። ኳስ ይዘን መጫወት አልቻልንም። እንደዚህ ዓይነት ሜዳ ላይ ፕሪምየር ሊግ ማጫወት ከባድ ነው። ጨዋታ እያለ ቀድሞ ሌላ ጨዋታ መደረጉ ራሱ ይበልጥ አበላሽቶታል።”
የፍቅሩ ወዴሳ ስህተቶች
“ኳስ ነው ፤ ይከሰታል። ግብ ጠባቂያችን ከዚህ ቀደም ብዙ ኳሶችን ሲያድን የነበረ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ አይነት ነገር ያጋጥማል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡