ደደቢት ከአራት ተጫዋቾቹ ጋር በስምምነት ተለያየ

ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ ከተሸነፉ በኃላ ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዳቸው ያረጋገጡት ሰማያዊዎቹ በቡድኑ ውስጥ የመሰለፍ ዕድል ላልተሰጣቸው በርካታ ወጣቶች የተሻለ የመሰለፍ ዕድል ለመስጠት በሚል ከአራት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት መለያየታቸው ታውቋል።

በዓመቱ ውድድር ዓመቱ መጀመርያ ቡድኑ ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ግብ ጠባቂው አዳነ ሙዳ በዓመቱ መጀመርያ ላይ ጋናዊው ረሺድ ማታውኪል በወረቀት ጉዳዮች ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ገብቶ ካደረጋቸው ጨዋታዎች በስተቀር በቂ የመሰለፍ ዕድል ያላገኘ ተጫዋች ነው።

ሁለተኛው ከቡድኑ ጋር የተለያየው በርካታ ቦታዎች ላይ መጫወት የሚችለው የቀድሞ የሶዶ ከተማ እና ሺንሺቾ ተጫዋች ዳግማዊ ዓባይ ሲሆን እሱም በክረምቱ ሺንሺቾን በመልቀቅ ነበር ሰማያዊዎቹን የተቀላቀለው ፤ በዓመቱ በአመዛኙ የአስልጣኞቹን ቀዳሚ ምርጫ የነበረው ተጫዋቹ ቡድኑን በበርካታ ቦታዎች አገልግሏል።

ሶስተኛው ከቡድኑ ጋር የተለያየው አማካዩ ኩማ ደምሴ ነው። በኢትዮጵያ መድን ፣ ባህርዳር ከተማ እና ደሴ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው አማካዩ በመጀመርያው ዙር ቡድኑን በቋሚነት ያገለገለ ሲሆን በሁለተኛው ዙር በጉዳት ምክንያት ቡድኑን እንደሚፈለገው አላገለገለም።

ሌላው ከቡድኑ ጋር በስምምነት የተለያየው በጥር የዝውውር መስኮት ከስሑል ሽረ ደደቢት የተቀላቀለው ግዙፉ አማካይ አሸናፊ እንዳለ ነው።
ከረጅም ዓመታት በኃላ ወደ እናት ክለቡ ተመልሶ የወራት ቆይታ የደረገው አማካዩ በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የአሰልጣኙን ፈለግ ተከትሎ ወደ ሰማያዊዎቹ ቤት በማምራት በርካታ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል ፤ ስሑል ሽረ ፣ አውስኮድ ፣ ቡራዩ የተጫዋቹ የቀድሞ ክለቦች ናቸው።

በቡድናቸው በርካታ ወጣት ተጫዋቾች የያዙት ደደቢቶች በተቀሩት የሊጉ ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድል ያልተሰጣቸው እንደነ አፍቅሮት ሰለሞን ፣ ዳንኤል ጌድዮን ፣ አብዱልሐፊዝ ቶፊቅ እና ሌሎች ተስፈኛ ወጣቶች የመሰለፍ ዕድል ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡