የአሰልጣኞች አስተያየት| ፋሲል ከነማ 4-0 ባህር ዳር ከተማ

የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ባህር ዳርን አስተናግዶ 4-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ዋንጫ ከፈለግክ ሱቆች ውስጥ ሞልተዋል፤ ገዝተህ ብትሄድ ነው የሚሻለው – ውበቱ አባተ (ፋሲል ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታዎች እያለቁ በመሆኑ እያንዳንዱ ጨዋታ ለኛ አስፈላጊ ነው። ደርቢ ከመሆኑ አንፃር እና ደረጃችንም አስቀጥለን ለመሄድ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ ለማድረግ ነው የሞከርነው። ቀድመን ግብ ማግባታችን ጨዋታውን በቀላሉ እንድንቆጣጠር አድርጎናል። ከዚህ በላይ የተሻለ መንቀሳቀስ የምንችልበት አቅም እንደነበር አይቻለሁ። ተጫዋቾቼ ግን በማስጠበቅ ላይ አተኩረዋል። ቢሆንም ጨዋታው ብዙም ከባድ አልነበረም።

ጨዋታው ሊለቀቅላቸው ይችላሉ ስለሚሉ ግምቶች

እውነት ለመናገር የሚለቁልን ቢሆን ኖሮ መስመሩ ላይም መቆም አልነበረብኝም። እኔ የማስበው ክለቡን ማዘጋጀት ነው። አራት እና አምስት ጎል ለመልቀቅ በጀት መድቦ ወደ ሜዳ የሚገባ ክለብ አለ ብዬ አላስብም። ባህር ዳር በጥሩ ስፖርታዊ ጨዋነት ነው የተጫወቱት። እስከ መጨረሻም ታግለዋል። ሌሎችም ጨዋታዎች በስፖርታዊ ጨዋነት ተጫውተን ማሸነፍ ነው የሚጠበቅብን። አለበለዚያ ዋንጫ ለማግኘት ይህን የሚያክል ሚሊዮን ገንዘብ መመደብ የለብህም። ዋንጫ ከፈለግህ ሱቆች ውስጥ ሞልተዋል። ገዝተህ ብትሄድ ነው የሚሻለው። ስለዚህ ከየትኛውም ቡድን ጋር ተወዳድረን ማሸነፍ ነው ያለብን።

“ሁለተኛው ዙር ሽንፈቶች የበዙብን በተጫዋቾች ጉዳት ነው” ጳውሎስ ጌታቸው (ባህርዳር ከተማ)

ስለጨዋታው

እንግዲህ እንደተመለከታችሁት ነው። መጀመሪያ አጀማመራችን ጥሩ ነበር። በአጋጣሚ የተቆጠረችብን ኳስ ተጫዋቾቼን ወዲያውኑ ነው ያወረደቻቸው። ብልጫ ወስደን በመጫወት ላይ እያለን ነው ጎሎች የተቆጠሩብን። ከእረፍት በኋላም ከፍተኛ ብልጫን ወስደን ነው የተጫወትነው።

የተጫዋቾች ጉዳት

ከባህር ዳር አምስት ተጫዋቾችን ሳንይዝ ነው የመጣነው። አሁንም ተጫዋቾች በመጎዳታቸው አላስፈላጊ ቅያሪዎችን አድርገናል። በሁለተኛው ዙር በጣም የተቸገርንበት ነገር ቢኖር ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ ጉዳት ማስተናገዳቸው ነው።

በየጨዋታው በርካታ ግቦች ማስተናገዳቸው

አንዳንድ ጊዜ እንዲህ አይነት ክስተቶች ይከሰታሉ። አንደኛ ፋሲል ለዋንጫ እየተፎካከረ ያለ ቡድን ነው። ሁለተኛ ቅድም እንዳልኩት ከአስር በላይ ተጫዋቾች ስለተጎዱብን ግቦችን እንድናስተናግድ አድርጎናል። እየተጫወትን ያለነው በአስራ አራት ተጫዋቾች ነው። ከነሱ ሶስቱ ግብ ጠባቂዎች ናቸው። ያለንበት ደረጃ አስተማማኝ ስለሆነ አሁን ያለው ነገር የሚያስከፋ አይደለም። ሁለተኛው ዙር ሽንፈቶች የበዙብን በተጫዋቾች ጉዳት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡