ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ደደቢትን በማሸነፍ ከመሪው ያላቸውን ርቀት አስጠብቀዋል

በ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቐለ ላይ ደደቢት ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደበት ጨዋታ በእንግዳው ቡድን 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት በአዳማ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ረሺድ ማታውኪል ፣ ዓብዱልዓዚዝ ዳውድ ፣ አሸናፊ እንዳለ እና ዓለምአንተ ካሳን በማስወጣት በሙሴ ዮሃንስ ፣ ዳዊት ወርቁ ፣ መድኃኔ ታደሰ እና ሙልጌታ ዓምዶም ተክተው ሲገቡ እንግዶቹ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት ድሬዳዋን ካሸነፈው ስብስባቸው ፓትሪክ ማታሲ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ሃምፍሬይ ምዬኖን በለአለም ብርሃኑ ፣ ሄኖክ አዱኛ እና ታደለ መንገሻ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ተመጣጣኝ ፉክክር እና ተቀራራቢ የኳስ ቁጥጥር በታየበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች አልፎ አልፎ ጥሩ የኳስ ቢታጀብም በሙከራ ደረጃ ግን እንግዶቹ ፈረሰኞቹ የተሻሉ ነበሩ። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የተከላካይ ክፍላቸው ወደ መሃል ሜዳ በማስጠጋታቸው እና ሁለቱም በተመሳሳይ የሜዳው ስፋት ለመጠቀም አዝማምያ ባለማሳየታቸው ምክንያት መሃል ሜዳው በርካታ ተጫዋቾች በመያዙ በተቀራረበ የቦታ አያያዝ ምክንያት ኳሶች ለመንሸራሸር አስቸጋሪ ነበር።

ናትናኤል ዘለቀ ከቅጣት ምት ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት እና በግብ ሙከራዎች ረገድ የተሻሉ የነበሩት የፈረሰኞቹ ግብ ለማስቆጠር ብዙ ግዜ አልፈጀባቸውም። በስምንተኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሐመድ በደደቢት ሳጥን ጠርዝ ላይ ያገኛትን ኳስ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኃላም በርካታ ዕድሎች የፈጠሩት ፈረሰኞቹ ጎሉ ከተቆጠረበት ደቂቃ ብዙም ሳይቆዩም ያለቀላቸው ዕድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም ታደለ መንገሻ ከ ሪቻርድ አርተር የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና ሪቻርድ አርተር ከአቤል ያለው አንድ ሁለት ተቀባብሎ መቶ ዳዊት ወርቁ በጥሩ ሁኔታ ተደርቦ ያወጣው የቅዱስ ግዬርጊስ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ከተቃረቡ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ሙሉዓለም መስፍን ከርቀት አክርሮ መቶት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰው ሙከራም የሚጠቀስ ነበር።

ከተጋጣሚያቸው በተመሳሳይ ጥሩ የኳስ ፍሰት የነበራቸው ሰማያዊዎቹ ምንም እንኳ በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ገብተው በርካታ የግብ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ከነዚህም መድኃኔ ብርኃኔ ኄኖክ መርሹ ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ እና ፉሴይኒ ኑሁ ከቅጣት ምት ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ። ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም ያብስራ ተስፋየ እና ፉሴይኒ ኑሁ ያደረጓቸው ሙከራዎች እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በተለይም ያብስራ ተስፋየ የለዓለም ብርሃኑ መውጣት አይቶ መቶት ናትናኤል ዘለቀ ከመስመር ያወጣው ኳስ ለጎል የቀረበ ነበር።

በ40ው ደቂቃ ሪቻርድ አርተር የተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ከበረኛው በመገናኘት በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ በርካታ የግብ ሙከራዎች ያልታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ምንም እንኳ በርካታ የግብ ዕድሎች ባይፈጠሩበትም ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር። በሙከራ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ ለግብ የቀረቡ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ታደለ መንገሻ በግል ጥረቱ በጥሩ ሁኔታ ወደ ሳጥን ገብቶ መቶት ሓድሽ በርኸ በግሩም ብቃት የመለሰው እና ናትናኤል ዘለቀ አክርሮ መትቶ ሓድሽ በርኸ የመለሰው ኳስ ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ቁጥር ወደ ጎል የደረሱት ሰማያዊዎቹም በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ያብስራ ተስፋየ ከቅጣት ያደረገው ሙከራ በጥሩነቱ የሚነሳ ነው። በ69ኛው ደቂቃም ፉሴይኒ ኑሁ አቤል እንዳለ በመስመር እየገፋ ገብቶ ወደ ሳጥን ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በ72ኛው ደቂቃ ሓድሽ በርኸ በአቤል ያለው ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ታመነ አስቆጥሮ ልዩነቱን መልሶ አስፍቶታል።

በመጨረሻዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች አጠቃላይ የጨዋታው እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ የታየበት ቢሆንም በ77ኛው ደቂቃ ሄኖክ መርሹ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ ያገኛትን ኳስ አክርሮ በመምታት እጅግ ግሩም ግብ በማስቆጠር የመጨረዎቹ ደቂቃዎች አጓጊ እንዲሆን አድርጎት ነበር። ሆኖም ከግቡ መቆጠር በኃላ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይታይበት በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡