አሰልጣኝ መሠረት ማኒ የተጓዘችበትን የህይወት ተሞክሮ የሚያሳይ “መሠረት ማኒ የብርታት ተምሳሌት” የተሰኘ መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ ታበቃለች።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት አሰልጣኝ በመሆን በሴቶች እግርኳስም ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ በመስራት ከፍተኛ ዝና እና ስም ያተረፈችው አሰልጣኝ መሠረት ማኒ ከልጅነት እስከ እውቀት ያሳለፈችውን የህይወት ጉዞ የሚያሳይ “መሠረት ማኒ የብርታት ተምሳሌት” የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባቢያን ልታቀርብ ነው።
198 ገፅ ያዘው ይህ መጽሐፍ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በድሬደዋ ከተማ በሚዘጋጅ ልዩ መርሐግብር የሚመረቅ ይሆናል። አሰልጣኝ መሠረት ማኒ ባዘጋጀችው መጽሐፍ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብላለች
“ያለፍኩበት ህይወት ብዙ ውጣ ውረዶች አሉበት። እነዚህ ውጣ ውረዶች ፣ ተሞክሮዎች እና ስኬቶች ለቀጣይ ትውልድ ማስቀመጥ መቻል አለብኝ። ከዚህ በተጨማሪም በሴትነቴ ብዙ ለፍቼ እና ደክሜ ነው እዚህ ደረጃ የደረስኩት። እነዚህ ነገሮች ዝም ብዬ ትቻቸው ተዳፍነው መቅረት የለባቸውም። የተወሰኑ ሰዎች አውቀዋቸው ብቻ እንዲቀሩም አልፈልግም። በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች የሚያውቁኝ በእግርኳሱ ብቻ ነው። ነገር ግን ከእግርኳሱ ውጪ በርካታ የሰራኋቸው ስራዎች አሉ። በመንግስት መስራያ ቤት እንዲሁም እራሴ የመሰረትኳቸው ለብዙ ልጆች ስኬታማነት የደከምኩባቸው ስራዎች ስላሉ ያንን ሌሎች ሰዎች እንደ ትምህርት እንዲወስዱት ማድረግ ያስፈልጋል። ሴት እህቶቼም እንዲማሩበት በማሰብ ነው መጽሐፉን ያዘጋጀውት”
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡