የአሰልጣኞች ገፅ ተመልሷል!
የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው በዚህ ገፅ የዛሬው እንግዳችን አሰልጣኝ ካሳሁን ተካ ናቸው። የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን፣ ኤሌክትሪክ፣ ኢትኮባ፣ ሙገር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ቆይታ ያደረጉ ሲሆን በዛሬው የክፍል አንድ መሰናዶ የአሰልጣኝነት ህይወታቸውን እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰጡትን ምላሽ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
በአሰልጣኝነት ካሳለፍክባቸው ክለቦች እንጀምር
★ እኔ፣ ሥዩም፣ ሰውነት እና አሥራት ማሰልጠን የጀመርነው ከፋብሪካ ቡድኖች ነው፡፡ እኔ በ1979 (እኤአ) ባገኘሁት የአሰልጣኝነት ፈቃድ ተነሳስቼ የተጫዋችነት ዘመኔ እንዳበቃ ታች ወርጄ አቃቂ ጨርቃ ጨርቅና <ዩኒ ፋይበር/ቃጫ> በተባሉ ክለቦች ሙያውን ሀ ብዬ ጀመርኩ፡፡ ያኔ ሁለት መቶ ብር የሚደርሰው ደመወዜ ብዙ ገንዘብ ነበር፡፡ አካባቢው ከሰፈሬ ሩቅ ቢሆንም ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ እየነዳሁ እየሄድኩ አሰልጥኜ እመለሳለሁ፡፡ በጊዜው የፋብሪካ ውድድሮች የደሩበት ዘመን ነበሩ፡፡ ጨዋታዎች እናያለን፤ አልፎ አልፎም አብረን እንጫወታለን፤ ቆየና የኢሰማ ቡድኖችም ተፈጠሩ፡፡ እነ ሥዩምና አሥራት <ትግል ፍሬ>ን ሲይዙ እኔ ደግሞ <ወደፊት>ን ተረከብኩ፡፡ ያን ጊዜ ቡድኖች በፋብሪካዎችና ኢንደስትሪዎች ዙሪያ ስለሚቋቋሙ የፋይናንስ ድርጀቶች የሆኑት ባንክና መድን እንዲሁም ትራንስፖርት <ወደፊት> ሲባሉ መብራት፣ ውሃና ጋዝ ደግሞ <እርምጃችን> የሚል መጠሪያ ተሰጣቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የሃምሳዎቹ ቡድኖች ምስረታ ሲታወጅ እኔ መድን ገባሁ፡፡ ቀጥሎ የወጣት ብሄራዊ ቡድኑ ተሰጠኝ፡፡ በሒደት ደግሞ የዋናው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኜ ተሾምኩ፡፡ በዚያውም የኢንስትራክተርነት ማዕረግ አገኘሁ፡፡ መሃል ላይ እጅግ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ያሳለፍኩበትና አዕምሮዬን በአግባቡ የተጠቀምኩበት የሙገርን ክለብ መራሁ፡፡ በዚያ ክለብ በ
ከመንግስቱ ወርቁ በኋላ በኢትዮጵያ ሁለተኛው የCAF ኢንስትራክተር ነህ፡፡ በምን መልኩ እዚህ ደረጃ ደረስክ?
★ በእርግጥ አሁን ያለውን ፎርማት አላውቅም፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጭቅጭቅ እንዳለ አስተውላለሁ፡፡ ‘እኔ እንዲህ ነኝ!’ ይሉሃል፡፡ ከ180 በላይ ኢንስትራክተሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ አሰልጣኞቹን የሃገር ውስጥ ኢንስትራክተሮች (Local Instructors) ብለህ መሰየም ትችላለህ፡፡ በእኛ ጊዜ በአፍሪካ እግርኳስ የኢንስትራክተሮች ቁጥር ሃያ ሁለት ብቻ ነበር፡፡ አንድ የCAF ቴክኒካል ዳይሬክተር እዚህ የመጣ ጊዜ እድሉን አገኘሁ፡፡ ሰውየውን በማስተባበር (co-ordination ) ስራ አግዘው ነበር፡፡ ዳይሬክተሩና እኔ ምስራቅ ጀርመን በሚገኝ ተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተምረናል፡፡ አንድ ቀን ምሳ እየተመገብን መወያየት ጀመርንና ‘ እኔ ኤኻፍ ነው የተማርኩት፡፡’ አልኩት፡፡ ‘እንዴ እኔም እኮ የዚያ ኮሌጅ ምሩቅ ነኝ፡፡’ አለኝ፡፡ የተማርነው በጀርመንኛ ቋንቋ ስለነበር በዚሁ ቋንቋ ሳናግረው እጅግ ተገረመ፡፡ ‘ታዲያ ለምንድን ነው የማታስተምረው?’ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ‘እኔ እንኳ እንዴት ማስተማር እንደሚቻል አላውቅም፡፡’ አልኩትና የትምህርት ማስረጃዎቼን ሰጠሁት፡፡ ሲቪዬን ከተመለከተ በኋላ ‘አንተ እኮ ብዙ መስራት የምትችል ሰው ነህ፡፡’ አለኝና አበረታታኝ፡፡ በተከታታይ እዚህ (Locally) የሚሰጡ ኮርሶችን አስተባበርኩለት፡፡ በመጨረሻ የስንብት ግብዣ ሲደረግ የፌዴሬሽኑ ባለስልጣናት በተገኙበት ሰልጣኞቹ ስጦታ ሲያበረክቱለት ምስጋና የማቅረብ ተራው ደረሰ፡፡ ” እኔ ብዙ ጊዜ ስጦታዎችን እቀበላለሁ፤ ዛሬ ግን በምላሹ ትልቅ ስጦታ ለእናንተ አበረክታለሁ፡፡” አላቸው፡፡ ሁሉም ‘ምን ይሆን ?’ እያሉ ሲጠብቁ ” እናንተን ሳስተምር ከጎኔ በመሆን ሲረዳኝ የነበረው ልጃችሁ በጣም ብቁና ጥሩ ጥሩ የምስክር ወረቀቶች የያዘ ባለሙያ ነው፡፡ ይህንን በቱኒዝ ለካፍ ኮንግረስ የቴክኒክ ክፍልና ዋናዋ አባላት አቀርባለሁ፡፡” አለ፡፡ እንዳለውም አደረገና ፈቃዴ ጸደቀልኝ፡፡ ከዚያም ወረቀቱን የወቅቱ የፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ጋሽ ተስፋዬ ገብረየስ ይዞ መጣ፡፡ በዓመቱ ወደ ኡጋንዳ ሄድኩ፤ ያኔ እንደዛሬው
በነገራችን ላይ ጋና ሁለት ጊዜ ሄጃለሁ፡፡ ኋላ ስሰማ በመጀመሪያው የጋና ጉዞዬ ትልቅ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር፡፡ ‘ እንዴት የኳስ ደረጃዋ እጅጉን ዝቅተኛ ከሆነ ሃገር አስተማሪ ይላክብናል? የአፍሪካ እግርኳስ ፌዴሬሽን/ካፍ/ እኛን ንቆናል ማለት ነው፡፡’ ብለው ሪፖርት ሁሉ ጽፈዋል፡፡ ‘ለማንኛውም እስቲ ሰውየውን እንየው!’ ይሉና ግለቱ በረደ፡፡ እኔ ደግሞ ሲሸልስ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ….. እና ሌሎች ሃገራት አስተምሬ ተመክሮ አዳብሬያለሁ፡፡ ሁሌም ኮርስ መስጠት ስጀምር ፕሮፌይሌን አልናገርም፤ ስጨርስ ነው የማሳውቀው፡፡ አጠቃላይ ሰልጣኞች ስለ አስተማሪያቸው የየራሳቸውን ግምገማ ያካሂዳሉ፡፡ እኔ በነዚያ ተማሪዎች እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ውጤት አስመዘገብኩ፡፡ ትዝ የሚለኝ ሁለት ተማሪዎች ሁልጊዜ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በአግባቡ መልስ አሰጣለሁ፤ የተግባር ስልጠናው ላይም እንዲሁ ይገረማሉ፡፡ ጋና ውስጥ <ዊኒባ> የሚባል የስፖርት ማዕከል አለ፡፡ በቴኒስ፣ በእጅ ኳስ፣ በመረብ ኳስ፣ በእግርኳስ፣…… እና በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች የሚያርፉበት ሃገር የሚያክል ማዕከል ነው፡፡ መኖሪያ አለው፤ መማሪያ ክፍሎች ተሟልተውለታል፡፡ እኔም የከረምኩት እዚሁ ስፍራ ነበር፡፡
በመጨረሻ ኮርሱ ሲያልቅ አንድ ቀን ማታ ሰዎቹ መጡና ” ይቅርታ አድርግልን! ” አሉኝ፡፡ አንደኛው ደግሞ ” እኔ ቡልጋሪያ ነው የተማርኩት፤ ማስተርስ ዲግሪም አለኝ፡፡ በአንተ <ክላስ> ውስጥ ብዙ አዳዲስ ትምህርቶችን ቀስመናል፤ እና እጅግ ተገርመናል፡፡ አመጣጣችን አንተን ለመታዘብ ነበር፡፡ ስናይ ግን ምንም እንከን አላገኘንብህም፡፡ እንዲህ አይነት ባለሙያዎች እያሏችሁ ታዲያ ለምንድን ነው እግርኳሳችሁ ያላደገው?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ስለ እኔ የጻፉትን ሪፖርትም አሳዩኝ፡፡ ስለ እውነት ነው የምላችሁ <ሳይንቲስት> ብለው ሁሉ ነው የሰየሙኝ፡፡ በእርግጥ አንደኛው አርዕስቴ (Topic) በሃገሪቱ በሚገኙ ጥሩ ጥሩ ባለሙያዎች ተገምግሟል፡፡ እነዚያ ሰዎች የምታስተምርበት ክፍል ገብተው ከተከታተሉ በኋላ ‘ ይሄን ነው እንዴ የሚያስተምረው?’ ብለው ሊያጣጥሉብህ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን እንዲያ ያለ ችግር አልገጠመኝም፡፡ እንዲያውም ለሁለተኛ ጊዜ ስሄድ በጣም ደስ አላቸው፡፡ ” በየሳምንቱ ብትመጣልን ደስታውን አንችለውም፡፡” ሁሉ ብለውኛል፡፡
ኢንስትራክተር ስትሆን CAF ይመድብህና ለሃገርህ እግርኳስ ፌዴሬሽንና ለራስህ Email ይደርስሃል፡፡ ከዚያም ፓስፖርትና ቪዛ የመሳሰሉ የጉዞ ሰነዶችን (Traveling Documents) በፌዴሬሽኑ በኩል እንዲጻፍልህ ታደርጋለህ፤ ትኬት ይላክህሃል፤ አበል ይቆረጥልህና ሄደህ አስተምረህ ትመለሳለህ፡፡ እኔ የማውቀው ይህን ሒደት ነው፤ አሁን ያለው ይለወጥ አይለወጥ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በእኛ ጊዜ ላይሰንሱ ከመዘጋጀቱ በፊት የየራሳችንን አርዕስት (Topic)/ መመረቂያ ጽሁፍ/ አዘጋጅተን አስረክበናል፡፡ የሆነ ጊዜ እንዲያውም (Zonal Instructor) እንፍጠር የሚል ሃሳብ መጣ፡፡ ለምሳሌ በምስራቅ አፍሪካ አስራ አንድ ሃገራት ይገኛሉ፡፡ በእያንዳንዱ ሃገሮች ደግሞ ኢንስትራክተሮች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ከአፍሪካ ኢንስትራክተሮች አንደኛው ሲመጣ እነዚህ የቀጠና ኢንስትራክተሮች የማስተባበሩን እና ሁኔታዎችን የማመቻቸቱን ኃላፊነት ይወጣሉ፡፡ ተጫዋቾችን በሚመለከት፣ የቢሮ ጉዳዮች፣ ሜዳ፣ ኳስ፣ ሆቴል፣ Accommodation እና መሰል እገዛዎችን ያደርጋል፡፡ ፈተናዎች ሲሰጡ ሰልጣኞችን በቋንቋ በኩል ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ከዚያ በኋላ የተቀየረውን አላውቅም፡፡
ስለ እግርኳስ የትየት ሃገራት ተማርክ?
★ ምዕራብ ጀርመን፣ ምስራቅ ጀርመን፣ ግብጽ
የእግርኳስ ትምህርቶችን መከታተል የጀመርከው ገና የተጫዋችነት ህይወትህ ሳይገባደድ ነው፡፡
★ አዎ! የፊፋን ላይሰንስ ያገኘሁት በ1979 (እ.ኤ.አ.) ተጫዋች ሆኜ ነው፡፡ እኔ፣ ሰውነት ቢሻውና ሥዩም አባተ አብረን ነበርን፡፡
ከመድን ክለብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለህ፡፡ በ1970ዎቹ፣ 1990 ፣ 1995 እና 1996 ክለቡን አሰልጥነሃል፡፡ በምትወደው ክለብ የነበረህን ቆይታ አውጋን
★ በመጀመሪያ ክለቡ ሲመሰረት እኔ ነኝ ያቋቋምኩት፡፡ ተጫዋችም ስለነበርኩ፥ ቡድን የመምራቱ ዝንባሌም ስለነበረኝ ተጫዋቾችን በአግባቡ መለመልኩ፡፡ የሚገርመው ያ ቡድን ዘመናዊ እግርኳስ ስለሚጫወትና አዝናኝ ስለነበር ” የእሁድ ፕሮግራም!” የሚል ቅጽል ስም ተሰጠው፡፡ ከፋብሪካ ቡድኖች ያገኘሁት የአዲስ ብስራት ወንድም፥ አብርሃም ብስራትን በጣም ቀጭን በመሆኑ የአስተዳደር ሰዎች ” እንዲያው ይሄ በምን እግሩ ነው ኳስ የሚመታው? ልትሰብረው እንዴ!” ሲሉኝ ፥ ” ስለሱ አታስቡ!” ብያቸው ውድድሩ ተጀመረ፡፡ አመራሮቹ አብርሃም ሲጫወት ሲያዩ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ እሱ የያዘውን የተጋይነት መንፈስ ማንም አያሳይም፤ ብዙ ብቃቶች ነበሩት፡፡ ረጃጅም ቅልጥሞች አሉት፤ ኳስ ያስጥላል፤ ቴክኒሺያን ነው፤ ግብ ያስቆጥራል፤… ኋላ ብሄራዊ ቡድን ተመረጠ፡፡ ተጫዋቾች ወደ ጣልያን ጠፍተው እኔ ሜዳ ገብቼ የተጫወትኩ ዕለት እርሱም አብሮ ጠፋ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ካናዳ ይኖራል፡፡ በመድን ምስረታ ወቅት እሱን የመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾች ብዙ ነበሩ፡፡
መድን ከምስረታው ጀምሮ ምርጥ ቡድን እንደነበረ ይነገርለታል
★ እንዴታ! ያ ቡድን በጣም የተደራጀ (Solid Team) ነበር፡፡ በወቅቱ ሲመንት የተባለው ቡድንም እጅግ ጠንካራ ተፎካካሪ ስለሆነ በሁለቱ ባላንጦች ጨዋታ ኳስ የ<መልስ ምት> የሚሆንበትን አጋጣሚ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ በቃ የጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታ (Pink-Ponk) ይመስልሃል፡፡ ልጆቹ ትክክለኛውን ስልጠና አግኝተዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በመሃል ጀርመን ሄጄ ስመለስም ብዙ ነገሮችን አስተምሬያቸዋለሁ፡፡ የዛኔም ጥሩ ይጫወቱ ነበር፡፡ በጣም የሚያሳዝነው በአሁኑ ወቅት ሁለተኛ ዲቪዚዮን ናቸው፡፡ ዘላቂነት (Continuity) ያለው ስራ ቢሰራ እንዲህ አይነቱን ውድቀት ማስወገድ ይቻላል፡፡ አውሮፓ ውስጥም ትልቅ ቡድን የመውረድ አጋጣሚ ይፈጠርበታል፤ ሆኖም ግን በዚያው ፈርሶ አይቀርም፤ ወዲያው ይመለሳል፡፡ ምክንያቱም ጊዜያዊ ውጤቱ የምስረታ አልያም የአደረጃጀቱን ታሪክ አይነካምና፡፡
መድንን ኢትዮጵያ ውስጥ ” አሉ!” የተባሉ አንጋፋና ስመ-ጥር አሰልጣኞች በሙሉ ተፈራርቀውበታል፡፡ ካሳሁን ተካ፣ ወርቁ ደርገባ፣ መንግስቱ ወርቁ፣ ሥዩም አባተ፣ ሃጎስ ደስታ፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል፣ ወንድማገኝ ከበደ፣ አስራት ኃይሌ፣….. በርካቶቹን የሃገራችን ውጤታማ አሰልጣኞች የቀጠረ ክለብ መጨረሻው እንዲህ የመሆኑ አበይት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
★ ክለቡ እነዚያን ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾች መተካት የሚችሉ አመራሮች አላዘጋጀም፡፡ ድሮ መንግስቱ ወርቁና እኔ ኢንሹራንስ ውስጥ እንሰራ ነበር፡፡ በ50ዎቹ ቡድኖች ምስረታ ጊዜ እኔ መድንን ሳደራጅ እርሱ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንደገና ሊያቋቁም ሄደ፡፡ እንዲያውም ጊዮርጊሶች በመድን ተሸንፈው እዚያው ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ቀሩ፡፡ ክለቡ የተጠናከረ የገንዘብ አቅም (Financial Status) ነበረው፡፡ ማንም ክለብ የአዲዳስ
ለአሰልጣኞች ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ልማድ በክለቡ ነበር ማለት ነው?
★ አዎ! ክለቡ የራሱ ሜዳና ዶርምተሪ ሰርቷል፡፡ ሌሎች ክለቦች ግን ስላልነበራቸው እንጦጦ እየሄዱ ልምምድ ይሰራሉ፡፡ ለተጫዋቾቹ የሚቀርበው የተመጣጠነ ምግብ ሲሆን እኔ ራሴ በሥነ-ምግብ ባለሙያዎች (Nutritionists) አማካኝነት የምግብ አይነቶች ዝርዝር (Menu) እንዲዘጋጅ አድርጌ በዚያ መሰረት ይመገባሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ አበረታች ግብዓቶች ተሟልተው ክለቡ ትልቅ ደረጃ ላይ ያልደረሰው ለምን ይመስልሃል?
★ የድርጅት ክለብ በመሆኑ ሥራ አስኪያጅ በተቀየረ ቁጥር የአሰራር ለውጥ ይፈጠራል፡፡ “ለስፖርት ይህ ሁሉ ወጪ የሚወጣው ለምንድን ነው?” የሚል አመራር ይመጣል፡፡ የመጀመሪያው አስተዳዳሪ እጅግ ተባባሪ ሰው በመሆኑ ሰራተኛ ቡድኑ እንኳ የፑማ
ከአሰልጣኝነት ሙያ ውጪ ምን ስራ ሰርተሃል?
★ አሜሪካ ውስጥ You go everywhere and you do everything you can.
እዚህ እያለህስ?
★ እዚህ እንኳ በኢንሹራንስ ዘርፍ በ Claim Department ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ በስራው ስለመኪና ጥሩ እውቀት ገብይቻለሁ፡፡ መድን ድርጅት እያለሁ የኢንሹራንስ ግምት ባለሙያዎች (Assessers) የመኪናዎቹን Mechanical ክፍሎች ፈትሸው ሲሄዱ እኛ ፋይሎቹን በደንብ እያገላበጥን እናያለን፡፡ መድን ስትቀጠር የአካዳሚ <ሲቪህ> ተብጠርጥሮ ታይቶ ነው የምትገባው፡፡ ያ በደንብ ጠቅሞኛል፡፡ ፈረንጅ ደንበኞች ስለሚመጡ ጥሩ የመግባባት ችሎታ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር የሚጻፈው በእንግሊዘኛ ነበርና፡፡ አሜሪካ እንደሄድኩ ብዙ ሰዎች “ምን ያህል ጊዜ ነው እዚህ ሃገር የቆየኸው?” ብለው ሲጠይቁኝ ” ገና ሰባት ወሬ ነው፡፡” ስላቸው ይገረማሉ፡፡ ልጆች ሆነን ስንማር መምህራኖቻችን ህንዳውያንና Peace Corps ነበሩ፡፡ አሽተው ነው የገሩን፤ ስለዚህ ብዙም የቋንቋ ችግር የለብኝም፡፡ እንግሊዘኛ በትክክልም ወንዝ የሚያሻግር መግባቢያ ነው፡፡
በአሰልጣኝነት ጊዜህ ቁጡና ስሜታዊ ነበርክ ?
★ አዎ! ግን አንዳንዴ!
የሙገሩን ከደጋፊ ጋር የተፈጠረ ግብግብ አስታውሰን…
★ ኦ! ከሱ ክስተት ጋር የተገናኘ የሚገርም ታሪክ ልንገራችሁ! አንድ ጊዜ ዩጋንዳ ሄጄ በካምፓላ የእግርኳስ ኮርሶችን ስሰጥ Role of Fans and Coaches…በሚል አርዕስት ስር ለተማሪዎቹ ያን አጋጣሚ እንደ ምሳሌ አነሳሁላቸው፡፡” ሜዳ ላይ ስሜታዊ ሆኜ ከደጋፊ ጋር የመጋጨት ሁኔታ ገጥሞኝ ቅጣት ተጣለብኝ፡፡ ሆኖም ያንን አልፌ እዚህ ደረስኩ፡፡” እያልኩ አስረዳኋቸው፡፡ ያንን ነው የማውቀው፡፡ ለካ ያን ንግግሬን ስሜን ጠቅሰው ኢንተርኔት ላይ በትነውታል፡፡ አሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ሁሉን ሒደቶች አልፌ በመጨረሻ መወሰኛ ችሎት ቀረብኩ፡፡ ያው እዚያ የምታቀርበው የፖለቲካ ጉዳዮችን ነው፡፡ ከዚያ ዳኛው ስለዚህ ጉዳይ እኔን ከጠየቀኝ በኋላ የአቃቤ ህጓን አስተያየቷን ለመስማት ፈቀደ፡፡ “ሌላ ማብራሪያ አንፈልግም፤ ያንተ መልስ መሆን የሚችለው <አዎ!> ወይም <አይደለም!> ብቻ ነው” አስጠነቀቀችኝ፡፡ ሰነዶቼን በጥልቀት መርምረውታል፤ “አንተ ጥሩ ስብዕና እንዳለህ ፋይልህ ይናገራል፤ ምንም ችግር አላገኘሁብህም፤ አሁን የመዋሸት እና ያለመዋሸት ጉዳይ ነው፡፡ ከዋሸህ ነገሮች ይበላሻሉ፡፡ ስለዚህ እውነቱን ተናገር፡፡” አለችኝ፡፡ ” ኢትዮጵያ እያለህ በእግርኳስ አሰልጣኝነት ስትሰራ ናዝሬት ከተማ ውስጥ ከአንድ ደጋፊ ጋር ተጋጭተህ ቅጣት ተጥሎብህ ነበር?” ብላ አፋጠጠችኝ፡፡ አይሁዳዊው ጠበቃዬ ይህኛውን ታሪኬን ስለማያውቅ ፊቱ በርበሬ መሰለ፡፡ “አዎ!” ብዬ ምላሼን ሰጠሁ፡፡ “ችግሩ በፍርድ ቤት ወይስ በእግርኳስ ማህበሩ ያለቀ ነበር?” ድጋሚ ሌላ ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ “በፌዴሬሽኑ!” አልኩኝ፡፡ ዳኛው አቃቤ ሕጓ ማብራሪያ ትፈልግ እንደሆነ ጠየቃት፡፡ “አያስፈልግም!” አለችው፡፡ ከዚያ <ግሪን ካርድ> ተሰጠኝ፡፡ የዚያኔ ” ኧረ እኔ አላቅም!” ብዬ ብዋሽ ኖሮ ያበቃልኝ ነበር፡፡ ጠበቃዬ ” እንዴት አልነገርከኝም?” ብሎ ተቆጣ፡፡ “እንዴ! እንዴት ብዬ ነው ስለ እግርኳስ የምነግርህ? እኔ የእግርኳስ ህይወቴ ከዚህኛው ጉዳይ ጋር እንደሚያያዝ በምን አውቃለሁ?” ብዬ ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት፡፡ ኋላ አቃቤ ህጓን ሄዶ ሲጠይቃት “I found the information from the internet.” አለችው፡፡ እና ይሄ ጥያቄያችሁ አሜሪካም መኖሪያ ፈቃዴን ለማግኘት የመጨረሻ ጥያቄ ሆኖ ቀርቦልኝ ለእኔ እንደ Turning Point ነበረ፡፡
…አጋጣሚው በ1992 አዳማ ላይ በተካሄደ የሙገር እና ቡና የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከአንድ ደጋፊ ጋር እስከመደባደብ ያደረሰህ ሲሆን ለአራት ዓመት ቅጣት ተዳርገህበትም ነበር፡፡ ቅጣቱ ተፈጻሚ ሆኖ ነበር እንዴ?
★ የአዳማ ቤንች አካባቢ ሆኜ ቡና አንድ ጎል ሲያገባ አንዱ ደጋፊ መጣና ገፈተረኝ፡፡ ትራኩ ላይ ከመውደቅ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡ ትንሽ ጠበቅሁትና ሲመጣ መታሁት፡፡ ከዚያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩና በሌለ ህግ ለአራት ዓመት ከሜዳ እንድታገድ የሚያስገድድ ቅጣት ተላለፈብኝ፡፡ በተጨማሪ አስር ሺህ ብር እንድከፍል ተወሰነብኝ፡፡ ሄድኩና ለሙገር ስራ አስኪያጅ ‘ይህንን ፍርድማ የትም ወስጄው ቢሆን ይግባኝ እጠይቅበታለሁ እንጂ እንዲሁ በቀላሉ አላልፈውም፡፡ እኔ በአስር ወር የማላገኘውን ገንዘብ ክፈል ይሉኛል እንዴ!’ ብዬ ስጮህ ኢንጅነር ግዛው ” አንተ ዝምበል! እኔ እከፍላለሁ!” አሉና እርሳቸው ከፈሉ፡፡
ይቀጥላል!
(በቀጣይ ሳምንት በሥልጠና እና ሲስተም ዙርያ የሚያተኩረውን ክፍል ይዘን እንቀርባለን)