በኢትዮጵያ ሴቶች ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ሀዋሳ ከተማ ጥረት ኮርፖሬትን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር መቀላቀል ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን ተቆጣጥረው ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሀዋሳዎች ደቂቃዎች አየገፉ በሄዱ ቁጥር ግን በተለይ ሳራ ኪዲ መዳከሟን ተከትሎ አስፈሪነታቸው ቢቀንስም የተጋጣሚያቸው ጥረት ኮርፖሬት ያልተቀናጀ አጨዋወት ግን ጫና እንዳይፈጠርባቸው አስተዋፅኦ አድርጓል። በ3ኛው ደቂቃ ነፃነት መና ሞክራ ታሪኳ በርገና መልሳው በጥረት ኮርፖሬት ተከላካዮች ርብርብ ግብ ከመሆን በዳነው ኳስ ወደ ግብ መድረስ በቻሉት ባለሜዳዎቹ በኩል 8ኛው ደቂቃ ላይ ቅድስት ቴቃ በተከላካዮች መሀል ሰንጥቃ የሰጠቻትን ኳስ በመጠቀም ነፃነት መና በጥሩ አጨራረስ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች። 28ኛው ደቂቃ ላይ ትመር ጠንክር ከቀኝ መስመር ያሻማችው ኳስ መሬት ላይ ሳያርፍ ሊድያ ጌትነት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክራ በአግዳሚው ለጥቂት የወጣችው በመጀመሪያው አጋማሽ በጥረት በኩል የምትጠቀስ ብቸኛዋ ሙከራ ነበረች። 31ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ጠባቂዋ ተሪኳ በርገና ድንቅ ብቃት ባይታከልበት ኖሮ መሳይ ተመስገን ከነፃነት መና ያገኘችውን ኳስ ወደ ግብ በመቀየር የሀዋሳን መሪነት የምታሰፋበት አጋጣሚ ነበራት። ምርቃት ፈለቀም ከሳጥን ውጪ የሞከረችው ኳስ አግዳሚውን ለትሞ ሊመለስ ችሏል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 1-0 መሪነት ወደ ዕረፍት አምርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው የመጡት ጥረት ኮርፖሬቶች ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል። ሆኖም ግብ ለማግባት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ኳስ ባገኙ ቁጥር በፍጥነት ተቀባብለው ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ የሚሰሯቸው የቅብብል ስህተቶች እና ወደ ሳጥን የሚጥሏቸው ረጃጅም ኳሶች በቀላሉ በሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች እንዲመለስባቸው ሆኗል። ባለሜዳዎቹም ከተከላካዮቻቸው ጥንካሬ እና ንቃት ውጪ ጥሩ ባልነበረው የመሀል እና የአጥቂ ስፍራቸው አልፎ አልፎም ቢሆን ሙከራዎችን ከማድረግ አልተቆጠቡም። በ50ኛው ደቂቃ ወርቅነሽ መሰለ በግራ መስመር ተነጥላ ወጥታ ለነበረችው ምርቃት ፈለቀ አመቻችታ ሰጥታት የጥረቷ ተከላካይ ቃልኪዳን ተስፋዬን አልፋ ወደ ጎል ብትሞክርም ታሪኳ በርገና አድናባታለች። ድንቅ ብታቷን ስታሳይ የነበረችው እና አንድ ለአንድ ከተጫዋቾች ጋር ስትገናኝ የግል ብቃቷን ተጠቅማ ኳሶችን ስታስጥል የነበረችው ሀሳቤ ሞሶ ከሳጥን ውጪ የተገኘውን የቀጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል ሞክራ ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቀሎ ኳሱን ሳትቆጣጠረው ቀርታ ትመር ጠንክር ብታገኘውም አባይነሽ ቀድማ የያዘችባት በጥረት ኮርፖሬቶችን አቻ ልታደርግ የምታስችል ሙከራ ነበረች። ከማዕዘን መሳይ ተፈሪ ያሻማችውን ቅድስት ቴቃ በግንባር ገጭታ ለጥቂት የሳተችው ኳስ ደግሞ በሀዋሳ በኩል የምትጠቀስ ሙከራ ነበረች። ሆኖም ጨዋታው ተጨማሪ ግቦች ሳያስተናግድ በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ባለሜዳዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡