በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ እየተወዳደረ የሚገኘው ነቀምት ከተማ ተጫዋች የሆነው ወንድወሰን ዮሐንስ በትላንትናው ዕለት በተነሳ ድንገተኛ ግርግር በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ አልፏል።
ተጫዋቹ ከክለብ አጋሮቹ ጋር በመሆን እራት ተመግበው ከሆቴል በመውጣት ላይ ሳሉ በአካባቢው የተነሳውና መነሻው ያልታወቀ ድንገተኛ ሁከት እስከ ቦንብ ፍንዳታ የደረሰ ሲሆን በዚህ አጋጣሚ ተጫዋቹ ከግርግሩ ለመሸሽ ሲሞክር ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ ሊያልፍ እንደቻለ ታውቋል። (ተጫዋቹ በግርግሩ ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ አልነበረውም)
ስለጉዳዩ የነቀምት ከተማው ዋና አሰልጣኝ ቾምቤ ገብርህይወት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ” በጣም አሳዛኝ ነገር ነው ያጋጠመን። ቦንቡ የፈነዳው እኔ ካለሁበት ቦታ ቅርብ በመሆኑ ተጫዋቾቹ ተረፍክ ወይ ብለው ደውለውልኝ ነበር። እነሱ ካሉበት ሆቴል በፍተሻ ከወጡ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር በሚሄድበት ጊዜ ነው ከመከላከያ ፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት ህይወቱን ያጣው። ወንድወሰን ከልጅነቱ ጀምሮ ነው የማውቀው። በጣም ጭምት ነው ቤተሰቡን የሚረዳ ነው። ሁለት መንታ ልጆች ይረዳል። እንጃ ለምን እንዲ እንደተደረገ፤ ወንድወሰን በቡድናችን ትልቅ ቦታ ነበረው። ለቡድኑ አባላት ለወላጆቹ እና ለወዳጆቹ በሙሉ መፅናናትን እመኛለሁ።” ብለዋል።
ወንድወሰን ዮሐንስ ትውልድ እና እድገቱ በሀዋሳ ኮረም ሰፈር አካባቢ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ የእድሜ እርከኖች ከተጫወተ በኋላ በስልጤ ወራቤ እና ኢትዮጵያ ውሀ ስራ (ኢኮስኮ) ሲጫወት ቆይቶ አሁን ወደሚገኝበት ነቀምት ከተማ አምርቶ እየተጫወተ የሚገኝ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ነበር። የተጫዋቹ አስከሬን ወደ ሀዋሳ እያመራ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በነገው ዕለትም በትውልድ ከተማው ሥርዓተ ቀብሩ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል።
ሶከር ኢትዮጵያ በተጫዋቹ ድንገተኛ እና አስደንጋጭ ህልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቡ እና ወዳጅ ዘመዶቸለ እንዲሁም ለክለቡ አባላት መፅናናትን ትመኛለች።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡