ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 0 ደደቢት ፡ ታክቲካዊ  ቅኝት

ዮናታን ሙሉጌታ

 

የ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀ ግብሮች ትላንት በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ቀጥለው ተካሂደዋል፡፡

በእለቱ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም እስከ ስድስተኛው ሳምንት ድረስ በሰበሰቡት ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ያደረጉት ጨዋታ በጉጉት የተጠበቀ ነበር፡፡  በውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆኗል፡፡ ይህን ጨዋታ የተመለከቱ አንዳንድ የጨዋታው እንቅስቃሴ ነጥቦችን እንደሚከተለው አቅርበንላቸኋል፡፡

ከላይ በምስል አንድ ላይ እንደተመለከተው ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሜዳ ይዘዋቸው የገቡት አሰላለፎች የተለያዩ ቢሆኑም የቡድኖቹ ባህሪ እና ለማጥቃት በተለይም የጐል እድሎችን ለመፍጠር የሚጠቀሙባቸው አማራጮች ተመሳሳይነት ነበሯቸው፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ የደደቢት ዋነኛ ተጋጣሚን የማጥቂያ መንገዶች ሁለቱ መስመሮች ናቸው፡፡  በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ቁልፍ ሚና ነበራቸው፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ወደኋላ በመመለስ ከተከላካይ አማካዮቹና ከመስመር ተከላካዮቹ እንዲሁም ከአጥቂ አማካዩ ምንያህል ተሾመ ኳስን በመቀበልና በኳሶች በተሻጋሪ ኳሶችን ወደ መሀል ለአጥቂው በመላክ እንዲሁም አልፎ አልፎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት የግብ እድሎችን ለመፍጠር የሚሞክሩባቸው እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚ መታየት ለቡድናቸው የጨዋታ ስትራቴጂ ቁልፍ መሣሪያ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳውን የጐን ስፋት በረጅሙ በመለጠጥ እና በተጋጣሚው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በሚኖረውን የተከላካዮችን አቋቋም መካከል ክፍተትን ለመፍጠርም የሚጠቅሙት የነዚህ የሁለቱ የመስመር አጥቂዎች አጨዋወት ነው፡፡

በደደቢት በኩልም የቡድኑን ዋና አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚን የመጨረሻ መድረሻ ያደረጉ እና አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ቁጥር በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እንዲደርሱ የታለሙ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ዋነኛ መነሻ የነበሩት ሁለቱ መስመሮች ናቸው፡፡ የደደቢት የመስመር አጨዋወት ዋነኛ ተዋንያኖች የአማካይ ክፍሉ ሁለቱ የመስመር ተሰላፊዎች ናቸው፡፡

ከጨዋታው መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ከላይ በምስሉ ላይ እንደተመለከተው ሁለቱ (የቀኝ እና የግራ) ክንፎች በሽመክት ጉግሳ እና ብርሃኑ ቦጋለ የተመሩ ነበሩ፡፡ የሁለቱ ተጨዋቾች በማጥቃትም ሆነ በመከላከልም ጊዜ ተጨዋቾች የሚኖራቸው እንቅስቃሴ ሚዛናዊነት እና ከተጋጣሚ ተጨዋቾች አቻ ወይም በተመሳሳይ ቦታ ላይ የሚገጥሟቸው የባላጋራ ቡድን ተሰላፊዎች ላይ የሚወስዱት የበላይነት የደደቢትን የጨዋታ አሸናፊነት የሚወስኑ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት በተጋጣሚ ተከላካዮች መካከል የሚኖረውን ክፍተት ለማስፋትና ለፈጣኑ አጥቂያቸው የመሮጫ ክፍተትን ለመስጠት የሁለቱ የመስመር አማካዮች ኃላፊነት ከፍ ያለ ነው፡፡ በጥቅሉ የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ስትራቴጂ ተመሳሳይ መሆን በጨዋታው ላይ የሚኖራቸውን የበላይነት የሚወስነው በሁለቱ መስመሮች ላይ በሚኖራቸው ብልጫ እንደሚሆን ግልፅ ነበር፡፡

im 2

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚው ላይ የተሳካ የበላይነት ማሳየት ችሏል፡፡  ይህም የበላይነት በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ቡድኑ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የታየ እንዲሁም በ 27 ደቂቃዋ የአዳነ ግርማ ጎል ነበር፡፡

በጨዋታው ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ወደ መስመር አጥቂዎቹ በሚላኩ ኳሶች እንዲሁም ከሶስቱ አጥቂዎች ጀርባ በነበረው ምንያህል ተሾመ አማካይነት ከመሀል ተነስተው ወደ መስመር በሚሄዱ ኳሶች ቡድኑ ከተጋጣሚው የተሻለ የጐል እድሎችን እንዲፈጥር እስችለውታል፡፡ እንዲሁም ከተከላካዮቹ ፊት የነበሩት የምንተስኖት አዳነ እና የተስፋዬ አለባቸው እንቅስቃሴ ብዙም ወደተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል የዘለቀ ያልነበረ በመሆኑ ፈጣኑን የደደቢት የአጥቂ ክፍል ከመሀል ተከላካዮቹ ጋር በመሆን ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል፡፡ ይህ የሁለቱ የተከላካይ አማካዮች በአብዛኛው በራሳቸው ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ ለመስመር ተከላካዮቹ አሉላ ግርማ እና ዘካሪያስ ቱጂ ቢያንስ እስከ ሜዳው ሁለት ሦስተኛ ክፍል ድረስ በመጠጋት ለመስመር አጥቂዎች ድጋፍ የመስጠት ነፃነትን ፈጥሮላቸው ነበር፡፡

የበሀይሉ አስፋ እና የራምኬ ሎክ ወደኋላ እየተመሰሱ ኳሶችን ለመቀበል የሚያደርጉት ጥረት ከመስመር ተከላካዮቹ ወደ መሀል ሜዳውን አለፍ ብሎ መገኘት እንዲሁም የምንያህል ተሾመ በቡድኑ የማጥቃት ክልል ውስጥ የነበረው ነፃ ሚና ለቡድኑ የመሀል ሜዳ የቁጥር ብልጫ እንዲኖረው ረድቶታል፡፡  ይህ እንቅስቃሴም የደደቢቶችን የመስመር ተከላካዮች በአብዛኛው በመከላከሉ ላይ እንዲያተኩሩና ከራሳቸው የግብ ክልል እንዳይወጡ አስገድዷቸዋል፡፡

ደደቢቶች ኳስን ከኋላ መስርተው ለመጀመር ያደርጉ የነበረውን ጥረት ሦስቱ የቅድስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ያደርጉባቸው በነበረው ጫና (pressing) ከጅምሩ ኳሱን ወደ ሁለቱ መስመሮቻቸው ለማድረስ አስቸጋሪ አድርጐባቸው ነበር፡፡ አልፎ አልፎም እዛው በመከላከል ወረዳቸው ላይ ሳሉ ኳስ ይነጠቁባቸው የነበሩ አጋጣሚዎች ለአደጋ ሲያጋልጣቸው ተስተውሏል ፡፡

ደደቢቶች በብዛት ለማጥቃት ይጠቀሙበት የነበረውን የቀኝ መስመርም ማለትም በሽመክት ጉግሳ በኩል ያለው መስመር በቅዱስ ጉዮርጊስ ተጨዋቾች በቁጥር እየበለጡ በመገኘት ሽመክት ኳስን ወደ አጥቂዎች ለማድረስም ሆነ ወደ ውስጥ ኳስን ይዞ ለመግባት የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች ከባድ አድርገውበት አምሽተዋል፡፡ ለዚህ የደደቢቶች የቀኝ የመስመር የማጥቃት ሂደት በቅዱስ ጉዮርጊስ ተጨዋቾች በቁጥር ብልጫ መዋጥ ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ጊዜ የምንያህል ተሾመ ወደ ግራው በመጠጋት ከ በሀይሉ አሰፋ ጋር በመሆን ሽመክት በመሀል ሜዳው አካባቢ ኳስ ሲይዝ የመሮጫ ክፍተት እንዲያጣ እንዲሁም ተጫዋቹ በማጥቃት ወረዳ ላይ ኳስ ሲይዝ ዘካሪያስ ቱጂ እና የተስፋዬ አለባቸው ክፍተትን የማጥበብ መከላከል እንደ ምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

በብርሃኑ ቦጋለ የሚመራውና በግራ በኩል ነበረው ሌላው የደደቢቶች የማጥቃት መስመር ግን ቡድኑ እንደ ማጥቂያ መንገድ ብዙም ሲጠቀምበት አልተስተዋለም ተጨዋቹም በአብዛኛው ወደመሀል ጠጋ ብሎ በመንቀሳቀስ አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ አሳልፏል፡፡ ይህ የተዳከመ መስመርም የተጋጣሚው የቀኝ መስመር ተሰላፊዎች ብዙ ጫና እንዳይሰማቸው አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ከተከላካይ አማካዩ ያሬድ ዝናቡ እስከ ሁለቱ አጥቂዎች ድረስ መሀል ለመሀል ያለውን ቦታ በመሸፈን እና ጨዋታ ለማቀጣጠል ጥረት ያደርግ የነበረውን ሳምሶን ጥላሁንም የምንተስኖትና የተስፋዬ ጥምረት የመጨረሻ ኳሶችን እንዳይፈጥር አድርገውታል፡፡

ይህንን ሰፊ የሜዳ ክፍል ሽፋን እንዲያግዘው ከሁለቱ አጥቂዎች አንዳቸው ወደኋላ ሲሳቡና የተወሰደበትን የቁጥር ብልጫ ሲያቀሉለትም አልታየም፡፡በዚህ መልኩ በመስመር እንቅስቃሴያቸው የተዘጋባቸው እና በመሀል ሜዳም የተበለጡት ደደቢቶች በሁለተኛው አጋማሽ ወግድረስ ታዬን በያሬድ ዝናቡ በመቀየር እና ሳምሶን በፊት ያሬድ ይጫወትበት የነበረውን ቦታ እንዲሸፍን እና በጥልቅ አማካይነት ሚና እንዲጫወት በማድረግ ተቀይሮ የገባው ወግ ደረስ መሀል ሜዳውን እያካለለ የመስመር አማካዮቹን እያገዘ እንዲሁም የሁለቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ አማካዮች ለመረበሽ ጥረት ሲያደርግ ተስተውለዋል፡፡ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ይህ እንቅስቃሴ ለደደቢቶች የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር እና ተጋጣሚያቸው ላይም ከመጀመሪያ ግማሽ በተሻለ መልኩ ጫና የመፍጠርን እድል ሰጥቷቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት ሦስት ተሰላፊዎች ወደፊት ለብቻ መነጠል እንዲሁም ከጀርባቸው የነበረው ምንያህልም ወደ አጥቂዎቹ የተጠጋ እነቅስቃሴ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የታቀደ ቢመስልም ነገር ግን ቡድኑን ለሁለት የተከፈለ የሚመስል ቅርፅ እንዲይዝ  እና ለደደቢቶች የበላይነት የበለጠ የተመቸ እንዲሆን አድርጐት ነበር፡፡  በተጨማሪም የቅ/ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮቻቸው እንደመጀመሪያው ግማሽ መሀል ሜዳውን በማለፍ ፈንታ ከኋላ ረጃጅምና ለመልሶ ማጥቃት የሚሆኑ ኳሶችን ለአጥቂዎች ለማድረስ ሲመክሩ ተስተውሏል፡፡

im 3

በሁለተኛው ግማሽ መጀመሪያ ደቂቃዎች የታየው ይህ የደደቢት የተነቃቃ እንቅስቃሴ ግን ቀስ በቀስ የጊዮርጊሶችየተረጋጋና አለፎ አልፎ ኳስን ወደኋላ መመለስና ኳስን ተቆጣትሮ ሰዓትን ለመግፋት እና ውጤትን ለማስጠበቅ በድንገትም ረጅም ኳሶችን በመጣል አደጋ ለመፍጠር በሚደረግ ሂደት ተተክቷል፡፡  በነዚህ ደቂቃዎች ላይ በተደጋገሙ እንቅስቃሴዎች አጥቂው አዳነ ግርማም ጭምር በጥልቀት ወደኋላ ሲመለስ እና ከ አማካዮቹ ጋር ኳስን ሲቀባበል ተስተውሏል፡፡ ደደቢቶች በጥቂቱ አግኝተውት ከነበረው ብልጫ ጐሎችን ለማግኘት ዮሴፍ አግዮኬን የሳሙኤል ሳኑሚ አጣማሪ በነበረው በጨዋታው ጥሩ ባልተንቀሳቀሰው ሄኖክ መኮንን ቀይረው አስገብተዋል፡፡  

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ናትናኤል ዘለቀን እና ብርያን ኡሙኒን በራምኬለክና በበኃይሉ አሰፋ ቀይረው በማስገባት ምን ያህል ተሾመን በቀኝ ብሪያን ኡሞኒን በግራ በኩል በማድረግ እንዲሁም ናትናኤል ምን ያህል ይጫወትበት የነበረው ቦታ እንዲይዝ በማድረግ ውጤታቸውን ለማስጠበቅ እንዲሁም የመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡  በብሪያን ኡሙኒ የመጨረሻ ሰዓት ጐልም የሰቡትን አሳክተዋል፡፡ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ተደምድሟል፡፡  

በዚህም መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16 ነጥብ ሁለተኛ ደደቢት ደግሞ በ11 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ይዘው ከ45 ቀናት በኋላ የሚደረገውን የሊጉን ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይጠብቃሉ፡፡

ያጋሩ