ብሄራዊ ቡድናችን የቻን ዝግጅቱን ዛሬ ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጥር ወር ለሚካሄደው ቻን 2016 ዝግጅት ጀምሯል፡፡ ቡድኑ ትላንት ሆቴል የተሰባሰበ ሲሆን ዛሬ ከቀትር በኋላ ልምምድ ሰርቷል፡፡

ከ10 ቀናት በፊት ይፋ ከሆነው የ30 ተጫዋቾች ምርጫ መካከል ለአለም ብርሃኑ እና ዳዊት ፍቃዱ በጉዳት ከቡድኑ ውጪ ሆነዋል፡፡ በግብ ጠባቂው ለአለም ምትክም የዳሽን ቢራው ደረጄ አለሙ ተመርጧል፡፡

በዛሬው ልምምድ ፕሮግራም ላይ 25 ተጫዋቾች ልምምዳቸውን ያከናወኑ ሲሆን ታሪክ ጌትነት እና አስቻለው ታመነ ቢገኙም ልምምድ ሳይሰሩ ቀርተዋል፡፡ አስቻለው ከደረሰበት ቀላል ጉዳት አገግሞ ወደ ልምምድ ለመመለስ እስከ 3 ቀን እረፍት እንደሚያስፈልገው ታውቋል፡፡ ሞገስ ታደሰ እና ስዩም ተስፋዬ አዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው የልምምድ ፕሮግራም ላይ ያልተገኙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ነገ 10፡30 ላይ ልምምዱን ሲቀጥል ማክሰኞ ወደ ሩዋንዳ የሚያመሩ 23 ተጫዋቾች ይፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተጨማሪ ተጫዋች እንደማይጠሩ ያስታወቁ ሲሆን ከ29 ተጫዋቾች መካከል እንደሚመርጡ አረጋግጠዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በወቅታዊ የብሄራዊ ቡድኑ ጉዳዮች ላይ ነገ በ8፡00 በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡

ያጋሩ