ሀ-20 | አአ ከተማ የምድብ ለ መሪነቱን ሲያጠናክር ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ ሀ መሪነትን ተረክቧል


በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ በምድብ ሀ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ በምድብ ለ ኤሌክትሪክ፣ አዲስ አበባ፣ ወልቂጤ እና አሰላ ኅብረት አሸንፈዋል።

በምድብ ለ 08:00 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ሀላባ ከተማን የገጠመው አዲስ አበባ ከተማ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 2-0 በማሸነፍ የምድብ መሪነቱን አጠናክሯል። ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት እና ወደ ጎል በመድረስ ብልጫ የነበራቸው አአ ከተማዎች በአላዛር ሽመልስ እና ያብቃል ፈረጃ አማካኝነት የጎል ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም የሀላባ ተከላካዮችን በማለፍ ጎል ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሀላባዎች በአአ ከተማ ብልጫ ቢወሰድባቸውም መከላከሉ ላይ በማተኮር በመልሶ ማጥቃት የጎል እድል ለመፍጠር አልፎ አልፎ ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል ቢደርሱም ግልፅ የግብዕድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። ጨዋታው በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ቀጥሎ 33ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ወደ ቀኝ ተከላካዮችን በማለፍ ኳሱን ወደ ፊት በመግፋት ከሳጥን ውጭ አላዛር ሽመልስ በግራ እግሩ አጠንክሮ ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጭ ወቶበታል። ከበረኛ ጀምረው ኳሱን በተሟላ ሁኔታ አደራጅተው ጫና የፈጠረቱ አዲስ አበባዎች በ43ኛው ደቂቃ በድጋሚ አላዛር ሽመልስ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያዳነበት የሚያስቆጭ የጎል አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽም ብልጫ ወስደው ማጥቃታቸውን የቀጠሉት አዲስ አበባዎች ጎል ለማግባት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ወደ ጎል ለመሄድ በሚያደርጉት የኳስ ቅብብሎች በሚፈጠሩ ስህተቶች ሀላባዎች በመልሶ ማጥቃት አደጋ ይፈጥሩባቸው ነበር። ለዚህም ማሳያ 65ኛ ደቂቃ አአ ከተማ ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ በፍጥነት ወደ ጎል የደረሱት ሀላባዎች እጅግ ለጎል የቀረበ ኳስ አግኝተው ምንተስኖት አየነ ወደ ላይ የሰደዳት በጨዋታው ሀላባዎች የፈጠሩት ብቸኛው የጎል ሙከራ ነው። ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የዋለው አላዛር ሽመልስ በግራ መስመር ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ጎል የሚጥላቸው ኳሶች አደጋ ከመሆናቸው ባሻገር እንቅስቃሴው በሜዳው የነበሩትን የሲሳይ አካዳሚ ታዳጊዎችን ያስደሰተ ነበር። ከዚህ በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች ጎል ፍለጋ በተሻለ ማጥቃት የቻሉት አዲስ አበባዎች በሁለት ደቂቃ ልዮነት ከቀኝ መስመር በሚሻገሩ ኳሶችን ብሩክ ሰሙ በግንባሩ በመግጨት የሞከራቸው አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

በቀኝ መስመር አድልተው በተደጋጋሚ ጎል እድል ለመፍጠር ተጭነው እንደመጫወታቸው ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ አዲስ አበባዎች 71ኛው ደቂቃ የመጀመርያውን ጎላቸውን አስቆጥረዋል። ከቀኝ መስመር በጥሩ ሁኔታ የተሻገረውን ኳስ የሀላባው ግብጠባቂ ሠላሙ በቀለ ኳሱን ለማውጣት ሲሻማ ያመለጠውን አሸናፊ ጉታ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ሀላባዎች ግብጠባቀያችን ኳሱን ለመያዝ ሲሞክር የአዲስ አበባ ተጫዋቾች ሚዛኑን አስተውታል በማለት ጎሉ የገባበትን መንገድ ተጫዋቾቹም የቡድኑ አባላት ተቋምዋቸውን አሰምተዋል። ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ያጠቁት አዲስ አበባዎች በአሸናፊ ጉታ የርቀት ኳስ ጥሩ ሙከራ አድርገው የነበረ ቢሆንም በዕለቱ በሀላባ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግብጠባቂ ሠላሙ በቀለ ድኖበታል። በመጨረሻም 86ኛው አላዛር ሽመልስ በሚገርም ፍጥነት ተከላካዮችን በማለፍ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ተቀይሮ ለገባው አብዱልሰመድ መሐመድ አቀብሎት ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በአዲስ አበባ 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ቀሪ ሁለት ጨዋታ እየቀረ ምድቡን በአምስት ነጥብ ልዩነት እንዲመራ አስችሎታል።

በምድብ ለ ረፋድ 4:00 ላይ ቦሌ በሚገኘው የልምምድ ሜዳው ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በታዲዮስ አዱኛ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል። መሪ የነበረው ሀዋሳ ከተማ ነጥብ በመጣሉም መሪነቱን በ34 ነጥቦች መረከብ ችሏል።

የ16ኛ ሳምንት ሙሉ ውጤቶች እና መርሐ ግብር

ምድብ ሀ

ቅዳሜ ሰኔ 1 ቀን 2011

ኢትዮጵያ ቡና 1-1 ሀዋሳ ከተማ
ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሲዳማ ቡና

እሁድ ሰኔ 2 ቀን 2011

ጥሩነሽ ዲባባ ከ ድሬዳዋ ከተማ (አሠላ/9:00)
ወላይታ ድቻ ከ አምቦ ጎል (ሶዶ/2:00)

ምድብ ለ
ቅዳሜ ሰኔ 1 ቀን 2011

ኤሌክትሪክ 2-1 አዳማ ከተማ
አአ ከተማ 2-0 ሀላባ ከተማ
ወልቂጤ ከተማ 2-1 ፋሲል ከነማ
አሰላ ኅብረት 2-1 አፍሮ ጽዮን


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡