ደደቢት ከሁለት ተጫዋቾች ጋር ተለያይቷል

ባለፈው ሳምንት ከአምስት ተጫዋቾች ጋር የተለያዩት ደደቢቶች አሁን ደግሞ ከሁለት የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ተለያይተዋል። ባለፈው ክረምት ባህርዳር ከተማን በመልቀቅ የቡድኑ የመጀመሪያ ፈራሚ የነበረው እንዳለ ከበደ እና ከታዳጊ ቡድን አድጎ ባለፉት ዓመታት ሰማያዊዎቹን ያገለገለው ዓለምአንተ ካሳ ከደደቢት ጋር የተለያዩት ተጫዋቾች ናቸው።

የደደቢት ታዳጊ ቡድን ውጤት የሆነው የአማካይ ክፍል ተጫዋቹ ዓለምአንተ ካሳ በዚህ ዓመት ቡድኑን በቋሚነት ያገለገለ ተጫዋች ሲሆን በጥቂት ጨዋታዎች ላይም አምበል ሆኖ አገልግሏል። በ2009 ወልዋሎ ዓድግራት ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የቡድኑ አባል የነበረው ተጫዋቹ በእግር ኳስ ህይወቱ ወደ ወልዋሎ አምርቶ ከተጫወተበት ዓመት ውጭ ሙሉ ግዜውን በደደቢት ነበር ያሳለፈው። አማካዩ በዚ ዓመት ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር አንድ ኳስም ለጎል አመቻችቶ አቀብሏል።

ሌላው ከቡድኑ ጋር የተለያየው የመስመር አማካዩ እንዳለ ከበደ ሲሆን እሱም በተመሳሳይ በዓመቱ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ነበር ያሳለፈው። እንደ ዓለምአንተ ካሳ ሁሉ የደደቢት ታዳጊ ቡድን ውጤት የሆነው ተጫዋቹ በተከታታይ ዓመታት ወልዋሎ እና ባህር ዳር ከተማ ወደ ፕሪምየርሊጉ ሲያድጉ የቡድኖቹ አንድ አባል የነበረ ሲሆን በውድድር ዓመቱ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።

ቡድኑ በዓመቱ ጥሩ ብቃት አሳይቶ ባለፈው ሳምንት በስምምነት የተለያየው ዳግማዊ ዓባይን ጨምሮ እስካሁን ድረስ ከስድስት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ተለያይቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡